AMN ታሕሣሥ 27/2017 ዓ.ም
ከቃል እስከ ባህል በሚል መሪ መልዕክት 2ኛው የብልፅግና ፓርቲ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ቅድመ ጉባኤ ውይይት በፌዴራል የሚገኙ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ዉይይት አድርጓል።
በውይይቱ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የፌደራል ተቋማት አስተባባሪ ዶክተር አለሙ ስሜ ናቸው፡፡
በመልእክታቸውም በብልፅግና ፓርቲ መሪነት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እሳቤዎች እና ልምምዶችን በተለወጠ እና አዲስ የሆነ የስራ ባህል በመተግበር የነዋሪውን ህይወት መለወጥ ያስቻሉ ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው ከምስረታው ጀምሮ በሁለንተናዊ መስኮች ለውጦችን ለማምጣት የህዝቦችን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የገባውን ቃል ከስኬት ለማድረስ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡
ከነባር እሳቤዎች በመውጣት ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ አሰባሳቢ እና አሳታፊ የፖለቲካ እሳቤን በመተግበር፣ የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ስርዓትን ወደ ስራ በማስገባት፣ በሰው ተኮር ተግባራት እና በአጠቃላይ ማህበራዊ ዘርፎች ለህዝቦች ተጠቃሚነት ቅድሚያ በመስጠትና በማረጋገጥ ረገድ ስኬት ተመዝግቧል፡፡
ፕሮጀክቶችን አቅዶ በፍጥነት በመተግበር እና ወደ ስራ በማስገባት፣ ስኬታማ ዲፕሎማሲን በማካሄድ እና በመሰል መስኮች ቃል በተግባር የተለወጠበት እና አዲስ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ባህል ለውጥ መምጣቱን የተናገሩት ዶክተር አለሙ ብልፅግና ፓርቲ በአንደኛው ጉባኤው የገባቸውን ቃሎች በተጨባጭ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ለቀጣይ ሁለት ቀናት በሚካሄደው የቅድመ ጉባኤ ውይይት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል ብሎም የታዩ ክፍተቶችን በቀጣይ ለማረም በሚያስችል ደረጃ በጥልቀት ይወያያሉ፡፡
የቅድመ ጉባኤ ውይይቶችና የአባላት ኮንፍረስ እስከ ጉባኤው መዳረሻ ድረስ በድምቀትና በከፍተኛ መነሳሳት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን መግለፃቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።