AMN – ሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም
ሙሉ ስሙ ኢባና ናስራዊ ላሚን ያማል ይሰኛል፤ በቀኝ ክንፍ ላይ ሲሮጥ ዕድሜውን የሚገምት ሁሉ ይሳሳታል።
የቀጣይ ዓመታት የዓለማችን ኮከብ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

አባቱ የሞሮኮ እናቱ ደግሞ የኢኳቶሪያል ጊኒ ተወላጆች ናቸው። እርግጥ እርሱ የተወለደው በስፔን ካታሎን የባርሴሎና ሜትሮፖሊታን ከተማ ሎብሬጋት ነው።
በዓለም ላይ የነገሡ ወጣት ተጨዋቾችን ያፈራው ላማሲያ አካዳሚ ውጤት ነው።
ላሚን ያማል ባለፈው ዓመት በአካዳሚው ያሳየው እንቅስቃሴ ከዕድሜው በላይ በመሆኑ ነበር በቀጥታ ወደ ባርሴሎና ዋናው ቡድን እንዲያድግ የተደረገው።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም ባርሳ ሪያል ቤትስን 4ለ0 ሲያሸንፍ ያማል ጋቪን ተክቶ የመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ጨዋታውን አደረገ።
በዚያን ጊዜ ዕድሜው 15 ዓመታት ከ9 ወራት ከ16 ቀን ነበር። ይህም በስፔን ላሊጋ ታሪክ በዕድሜ 5ኛው ትንሹ ተሰላፊ እንዲሁም ለባርሴሎና ደግሞ ከአርማንዶ ሳጊ ቀጥሎ ያለውን ቦታ አስያዘው።
የባለፈው ዓመትን በላሊጋ ዋንጫ ድል አጠናቀቀ። ለዚህ ዓመቱ ውድድርም መዘጋጀት ጀመረ።
ነሐሴ 2015 ዓ.ም በላሊጋው ካዲዝን 2ለ0 ሲያሸንፉ ተሰልፎ ዓመቱን በድል ጀመረ።
ዘንድሮ ባርሴሎና እንደ ቡድን በዋንጫ የታጀበ ዓመት ባያሳልፍም እርሱ በግሉ ግን ድንቅ ክህሎቱን ለእግር ኳስ ወዳዱ አሳይቷል።
ከእግር ኳሱ ጎን ለጎን ትምህርቱም ላይ ታታሪ ነው። ቀን ቀን እግር ኳስ ምሽት የትምህርት ጥናት የላሚን ያማል መገለጫ ናቸው።
በኤል ክላሲኮ ጨዋታ ላይ የተሰለፈ ትንሹ ተጨዋች፣ ግብ አመቻችቶ የሰጠ ትንሹ ተጨዋች፣ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የተሰለፈ ሁለተኛው ትንሹ ተጨዋች፣ የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጨዋች ብቻ በርካታ ክብረ ወሰኖችን ሰባብሯል – ከሁለት ቀናት በኋላ 17ኛ ዓመት ልደት በዓሉን የሚያከብረው ላሚን ያማል።
እነዚህና ተጨማሪ በርካታ ሪከርዶችን የሰባበረው ላሚን ያማል የስፔን ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሊዊስ ዴ ላ ፎንቴ ዕይታ ውስጥ ገባ።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ መስከረም ወር ላይ ስፔን ከጆርጂያ እና ቆጵሮስ ጋር ባደረገቻቸው የአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ላሚን ያማልን ጠሩት።
በ16 ዓመቱ ከ50 ቀናት ለሀገሩ የመጀመሪያ ጨዋታውን አደረገ፣ ግብም አስቆጠረ።

በእንቅስቃሴው የተደሰቱት ፎንቴ በሰሞኑ የአውሮፓ ዋንጫም የቋሚ ተሰላፊነትን ሚና ሰጥተውታል።
ስፔን በሩብ ፍጻሜ ጀርመንን 2 ለ 1 አሸንፋ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ስታልፍ ያማል ለግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።
ትናንት ምሽት ስፔን ፈረንሳይን 2ለ1 አሸንፋ የፍጻሜ ትኬቷን ስትቆርጥም የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል።
እንደ ዊሊያም ሳሊባ፣ ዳዮት አፓሜካኖ እና ቲኦ ኸርናንዴዝን የመሳሰሉ ጠንካራ ተከላካዮች ያለውን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ፋታ ሲነሣቸው አምሽቷል።
ስፔንን ከተመሪነት ወደ አቻነት የቀየረችውን ማራኪ ግብ ያስቆጠረውም ይኸው በ17 ዓመት ልደት በዓሉ ዋዜማ ላይ የሚገኘው ላሚን ያማል ነው።
የእግር ኳስ ተመልካቹን ቀልብ ሰክዞ የያዘው ላሚን ያማል የመጪዎቹ ዓመታት ኮከብ ይሆናል ሲሉ ብዙዎች ከወዲሁ ግምት ሰጥተውታል።
የስፔን እና ባርሴሎና መተማመኛ ላሚን ያማል ሀገሩን ለአውሮፓ ዋንጫ አራተኛ ድል ያበቃ ይሆን? ለራሱም ዋንጫውን የ17ኛ ዓመቱ ስጦታ ያደርገው ይሆን? በመጪው እሑድ መልስ የሚያገኝ ጥያቄ ነው።
በታምራት አበራ