AMN – ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም
በ2016 በጀት ዓመት በትምህርት ዘርፉ ወጤት መገኘቱን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የ 2016 የትምህርት ዘመን ዕቅድ አፈጻጸምና የ2017 ዕቅድ ላይ ከትምህርት ቤት አመራሮችና ባለሞያዎች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ በስድስተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ፈተናዎች የተመዘገው ውጤትም ካለፉት አመታት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛው መሆኑ ተገልጿል።
በዓመቱ የስድስተኛ ክፍል የሚኒስትሪ እና የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዎችን ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውም ተገልጿል።
90 በመቶ በላይ የስድስተኛ ክፍል እና 87 በመቶ በላይ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ሀምሳና ከዚያ በላይ አምጥተዋል ነው የተባለው።
በዚህ ረገድ አመርቂ ውጤቶች ቢመዘገቡም ወደ ፊት የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸውም ተመላክቷል።
በውይይቱ ላይ የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ እንደገለጹት ትምህርት በውጤት የሚለካ እና የሁሉንም ርብርብ የሚፈልግ ነው።
የጋራ ርብርቡ በዓመቱ ለውጥ ያመጣ ነው ያሉ ሲሆን በተለይ “ትምህርት ለትውልድ” በሚለው ዘመቻ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የተሠራውን ሥራ አንስተዋል።
በቀጣይ በተለይ ሂሳብ እና እንግሊዝኛ ትምህርቶች ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ሥነ-ምግባር ሁኔታ በዓመቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰበት ዓመትም እንደነበር ዶ/ር ዘላለም አንስተዋል ።
ይህን አስጊ የሥነ-መግባር ችግር ፈትሾ በጋራ መቅረፍ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
በዓመቱ ውጤታማ መምህራኖች ብዙ እንደመሆናቸው ሁሉ ኃላፊነታቸውን ባግባቡ መወጣት ያልቻሉ እንደነበሩም ተናግረዋል። ይሄም በትኩረት መታየት ያለበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ውይይቱ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በቀጣይ የ2017 ዕቅድ ላይም ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።
በዓለማየሁ አዲሴ
#Addisababa
#Ethiopia
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!