በ2017 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት ከወጪ ንግድ ከ1ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል፡-የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

You are currently viewing በ2017 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት ከወጪ ንግድ ከ1ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል፡-የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

AMN- ጥቅምት 18/2017 ዓ.ም

በ2017 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት ከወጪ ንግድ ከ1ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም እየገመገሙ ነው፡፡

በመድረኩ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ባለፉት መቶ ቀናት የሚኒስቴር መ/ቤቱ እና የተጠሪ ተቋማት የአፈፃፀም ውጤቶች ጎልተው የወጡበትና በርካታ ስኬቶችና ድሎች የተመዘዘገቡበት የአፈፃፀም ወቅት እንደሆነ አንስተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 1ኛ ሩብ ዓመት ሚኒስቴሩ ክትትል ከሚያደርግባቸው ምርቶች የወጪ ንግድ 1 ቢሊዮን 508 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱንና ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ700 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለው አንስተዋል፡፡

ከ900 ሺ ባለይ ኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት መሰጠቱን ሚኒስትሩ ገልፀው ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ450 ሺ ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ገበያውን ለማረጋጋት አማራጭ ገበያዎችን ከማስፋፋት አንፃር በሩብ ዓመቱ 88 አዳዲስ የሰንበት ገበያዎች የተመቻቹ መሆኑንና በአጠቃላይ 1 ሺ334 የሰንበት ገበያዎች ተመቻችተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ በህገወጥ ንግድ ላይ በተደረገው የክትትልና ቁጥጥር ስራ 103 ሺ በሚሆኑ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ በመውሰድ ገበያው እንዲረጋጋ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ከጥራት መሰረተ ልማት አንፃር ለ9 ዓመታት ግንባታው ሲጓተት የነበረው የህንፃ ግንባታና የላቦራቶሪ ተከላ ስራ በሩብ ዓመቱ በተደረገው ክፍተኛ ርብርብ ግንባታው ተጠናቆ ለምረቃ ዝግጁ መሆኑን ሚኒስትሩ መናገራቸውን ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review