በ2017 ዓ.ም አንደኛ ሩብ ዓመት ከፍተኛ ውጤት ባስመዘገበው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ልምድ ልውውጥ ተካሄደ

AMN-ታህሣሥ 15/2017 ዓ.ም

በ2017 ዓ.ም አንደኛ ሩብ ዓመት በሪፎርም ተግባራት አፈጻጸም በተደረገ ድጋፍና ክትትል ከፍተኛ ደረጃ ባስመዘገበው አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ልምድ ልውውጥ ተካሄዷል።

በመርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱን ጨምሮ የቢሮ ማኔጅመንት አባላት፣ የክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም የክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት የሪፎርም ስራ አስተባባሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ፣ ትምህርት ጽህፈት ቤቱ የጋራ የሆነና የተቀናጀ የአሰራር ስርዓት ዘርግቶ ባከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ የሆነበት መንገድ ሌሎች ተሞክሮ መውሰድ የሚችሉበት በመሆኑ የልምድ ልውውጥ መርሀግብሩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ከዋና ስራ አስፈጻሚው ጀምሮ ለትምህርት ሴክተሩ ከፍተኛ በጀት እየመደበ ትምህርት ቤቶችን በፍጥነት በመገንባት ለአገልግሎት እንዲውሉ እያደረጉበት የሚገኘው መንገድ የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን አመላክተዋል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ሚጄና በበኩላቸው፣ የክፍለ ከተማው አስተዳደር ለትምህርት ሴክተሩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸውዋል፡፡

ከትምህርት ጽህፈት ቤቱ ጋር በቅንጅት በመስራት የትምህርት ቤቶች ደረጃም ሆነ የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል እየተሰራ እንደሚገኝ መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review