AMN- ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም
በ2017 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአንድ ሚሊየን በላይ ዜጎችን በማሳተፍ የበርካታ ዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ የ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መዝጊያ እና የ2017 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃግብር እያካሄደ ነዉ።
በክረምቱ በጎ ፈቃድ አገልግሎት 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መከናወኑ በመድረኩ ተገልጿል።
በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 18 መርኃ-ግብሮች የተከናወኑ ሲሆን፤ የቤት እድሳትና ግንባታን ጨምሮ የደም ልገሳ፣ ማዕድ ማጋራት፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የትራፊክ አገልግሎትና ሌሎች መሆናቸው ተመላክቷል።
በዚህም ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ በጎ ፈቃደኞች ተሳትፈዋል።
“በጎ ፈቃደኝነት ለማኅበረሰብ ለውጥ!” በሚል መሪ ቃል ተግባራዊ የሚሆነው ፕሮግራሙ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ የላቀ አበርክቶ እንደሚኖረው ተገልጿል።
አስር ዐበይት መርሃ ግብሮችንና 13 ንዑሳን ተግባራትን ያካተተው ይህ ፕሮግራም ከአንድ ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞችን ያሳትፋልም ተብሏል።
በሀብታሙ ሙለታ