በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚ ኩራ ክ/ከተማ ቦሌ አራብሳ አካባቢ የተገነባው የለሚ እንጀራ መጋገሪያ ማዕከል በቀጥታ ከማከፋፈያ ጣቢያ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ የሚያስችል የኤሌክትሪክ መስመር ግንባታ በ32 ሚሊየን ብር ወጪ እያከናወነ መሆኑን የምስራቅ አዲስ አበባ ዲስትሪክት ዲስትሪቢውሽን ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ድሪባ ገልፀዋል።
የኤሌክትሪክ መስመር ግንባታውን ማከናወን ያስፈለገው በ2015 ዓ.ም ተዘርግቶ የነበረው 15 ኪ.ቮ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር የእንጀራ መጋገሪያ ማዕከሉ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እንዲሰጥና የኃይል መዋዠቅና መቆራረጥ እንዳይከሰት ለማድረግ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።
ማዕከሉን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ 5 ኪ.ሜ የመካከለኛ መስመር፣ አራት ባለ 1 ሺህ 250 ኪሎ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች እና 106 የመካከለኛ መስመር የኮንክሪት ምሰሶዎች ተከላ ስራ መከናወኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።