ቡሄ፣ ልጅነት እና ትዝታው

You are currently viewing ቡሄ፣ ልጅነት እና ትዝታው

ቡሄ፣ ልጅነት እና ትዝታው

ህጻናት የተቆራረጡ ብረቶችን እና የጠርሙስ ክዳን ቆርቆሮዎች እየሰበሰቡ ነው። ዱላ የሚሆን እንጨት ፍለጋ ወዲያ ወዲህ ማለት ጀምረዋል፡፡ አዳዲስ ጅራፎችን እየፈተሉ ነው፡፡ ምክንያቱም ቡሄ ደርሷል፡፡ ቡሄ ሲደርስ አዲስ አበባ ሌላ ውበትና ድምቀት ትላበሳለች። በጋራ የሚጨፍሩ ህጻናት በጎዳናዎች ላይ መታየት ይጀምራሉ፡፡ በእንጨት ጫፍ ላይ የጠርሙስ ክዳን (ቆርኪ) መትተው ከመሬቱ ጋር በማጋጨት የሚፈጠረውን ድምጽ ለጭፈራው ማድመቂያ ያደርጉታል፡፡

ሆያ ሆዬ ሆ

መጣና በዓመቱ

አረ እንደምን ሰነበቱ

ሆያ ሆዬ

ሆያ ሆዬ ጌታ ጠንበለል

ዝናቡ መጣ ወዴት ልጠለል

አባብዬ ቤት እጠለላለው

ሙልሙል ዳቦዬን ይዤ እሄዳለው… ይላሉ፡፡

ህጸናት በቡሄ ወቅት ጅራፍ እያጮሁ ሆያ ሆዬ ሲጨፍሩ ከታላላቆች ምርቃትና ሽልማት ይቀበላሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ሙልሙል ይበረከትላቸዋል፡፡ በእርግጥ አሁን አሁን ልጆች አጋጣሚውን ገንዘብ ለማግኘት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡ ይህ ከሆያ ሆዬ ትውፊታዊ ስርዓት እና ባህል ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመለስ ቡሄ ተናፋቂ በዓል ነው፡፡ የጅራፉ ድምጽ፣ የችቦው ብርሃን የልጆቹ ጭፈራ እና ጉጉት በየዓመቱ እንደ አዲስ የሚሰማና የማይጠገብ ያደርገዋል። በአጠቃላይ ከነሃሴ ወር ጀምሮ የሚከበሩት ቡሄ፣ እንቁጣጣሽ፣ መስቀል፣ ኢሬቻ… የተስፋ እና የደስታ የልጆችም መቦረቂያ ናቸው፡፡ “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” የሚባለውም ለዚሁ ነው፤ የዝናቡና የጨለማው ወቅት ማለፉን፣ የብርሃንና የደስታ እንዲሁም የልምላሜ ዘመን መምጣቱን ለመግለጽ፡፡

በአዲስ አበባም ሆያ ሆዬ የሚጨፍሩ ልጆችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ በተለይ ህጻናት ከእኩዮቻቸው ጋር ስለሚጨፍሩ፣ ከቤት የመውጣት እድል ስለሚፈጥርላቸው፣ ስጦታዎችንም ስለሚቀበሉ በልዩ ሁኔታ ወቅቱን ይጠብቁታል፡፡ በጋራ ተሰብስበውም እንዲህ በማለት ይጨፍራሉ፡፡

የቡሄ ዳቦ የሚሉት ሙልሙል

ጎበዝ ተሰብሰብ ቡሄ እንበል።

ሆያ ሆዬ ጉዴ… እያሉ በሩ ጋር ይጨፍራሉ፡፡ በር እስከሚከፈት ወደ ውስጥ መግባት እስከሚፈቀድላቸው ሞቅ ባለ ድምጽ ይጨፍራሉ፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ “ቆይ በደንብ ይጨፍሩ” በሚል በር ቶሎ ላይከፈትላቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም በዓመት አንዴ የሚመጣ እድል በመሆኑ ባላቤቶቹም የልጆቹን ጭፈራ ማየትና መዝናናት ይፈልጋሉ።

ልጆቹ ሆያ ሆዬ በሚጨፍሩበት ወቅት ወደ ቤት የሚገቡት ሲፈቀድላቸው ብቻ ነው፡፡ ከዛም በሩ ተከፍቶ እንዲጨፍሩ ሲፈቀድላቸው የቤቱን ጌታና እመቤት በግጥምና በዜማቸው ማወደስና ማሞገሱን ይያያዙታል… በዚህም መሰረት የቤቱን አባወራ…

ወይ የኔ ጌታ የሰጠኝ ሙክት

እግንባሩ ላይ አለው ምልክት

መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት

በጌታዬ ቤት በጉልላቱ

ወርቅ ይፍሰስበት ባናት ባናቱ።

የኔማ ጌታ ጌታ ነው ጌታ

ሲቀመጥ ሲያምር ሲቆም ሲረታ።

የኔማ ጌታ የሰጠኝ ላም

አስር ዓመትዋ ኖረች በዓለም… እያሉ ያወድሳሉ፡፡ የሚወደሰው አባወራው ብቻ አይደለም፡፡ እመቤቲቱም በግጥምና በዜማ ይወደሳሉ፡፡

የኔማ እመቤት መጣንልሽ

የቤት ባልትና ልናይልሽ።

የኔማ እመቤት የጋገረችው

የንብ እንጀራ አስመሰለችው።

የኔማ እመቤት ብትሰራ ዶሮ

ሽታው ይጣራል ገመገም ዞሮ… እያሉ ያወድሳሉ፡፡ እንዲህ እያሉ ከጨፈሩና የሚሸለሙትን ከተሸለሙ በኋላ ለዓመቱ በሰላም እንዲያደርሳቸው ተመኝተው ተመራርቀው ይለያያሉ።

በእርግጥ በአዲስ አበባ ግጥሞቹ እንደየወቅቱ የሚቀያየሩበት ሁኔታ አለ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ቤትና መኪና ወይም በወቅቱ በብዙዎች ዘንድ የሚፈለግ ብርቅ የሆነ ነገርም ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ብዙ ጊዜ፡-

ሆያ ሆዬ ሆ ሆያ ሆዬ ሆ

እዚህ ማዶ አንድ ባላ ሆ

እዚያ ማዶ አንድ ባላ ሆ

የእኛማ ጋሸ ሆ ባለቪላ… በማለት ይጨፍራሉ፡፡

በነገራችን ላይ ሆያ ሆዬ እና ቡሄ በሀገራችን ሥነ ጽሑፍ እና ሙዚቃ ውስጥ ብዙ ስፍራ ይዞ እናገኘዋለን፡፡ ይህን ድንቅና አይረሴ የልጅነት ጊዜ እና ትዝታን ከትበው ካስቀመጡ ሰዎች ውስጥ ደራሲ ዘነበ ወላ አንዱ ነው፡፡ ዘነበ “ልጅነት” በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ቡሄና ሆያ ሆዬ በልጆች ዘንድ ምን እንደሚመስል አትቷል። በመጽሐፉ ውስጥ “መጣና ጌታችን ላመት ክብራችን” በሚል ርእስ ገጽ 101 ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

ሆያ ሆዬ ሆ

የእኔ ጌታ ሆ

ጌታ ነው ጌታ ሆ

ጌታ ጠምበለል ሆ

ዝናቡ መጣ

 ሆ ወዴት ልጠለል…. በሚል ጽሑፉን የሚጀምረው ደራሲው፣ “ሰኔ ሰላሳ የፈተና ውጤታችንን ካወቅን በኋላ ትምህርት ቤታችን ይዘጋል። ሐምሌ ተጠናቅቆ ታላቅ ፍስሐ ይዞልን የሚመጣው ወር ነሐሴ ነበር። ነሐሴ 13 ቀን ቡሄ ነው። ቀደም ብለን እንዘጋጃለን። ጅራፍ በሰፈራችን እዚህም እዚያም ይጮሃል። ትልልቅ ሰዎች የትም ሆነው ‘ኡ! ይጩህባችሁ!…’ እያሉ ሲያማርሩ ይሰማሉ። እኛ ግን ትንሽ ራቅ ብለን አካባቢውን በጅራፍ ጩኸት እናደበላልቀዋለን…” እያለ ይቀጥላል።

ዘነበ “ቡድናችን ከዓመት ወደ ዓመት ይለዋወጣል። ቁጥራችን አንዳንዴ ይበዛል፣ አልያም ያንሳል። ዘንድሮ እኔ፣ ጎቢጥ፣ መኩዬ ቀጫጫው፣ ሴምላል፣ ቀጢሳው፣ ሻቃ፣ ይጥና፣ ፑሉቶ፣ ዶሮ፣ ውሮና ጎይቶም አሻሮ የአንድ ቡድን አባል ለመሆን ወሰንን። ዓለምነህንና ወንድሙን ደምስን አናስገባም አልናቸው። ሁለቱ በጉልበት ከእኛ ስለሚበልጡ አይን በአይን ያጭበረብሩናል። ስለምንፈራቸው በአይናችን ያየነውን ስሙኒ ዲናሬ ነው ሲሉን ማመኑ ለደህንነታችን ይበጃል” በማለት የቡሄ ሰሞን ጭፈራ አይረሴ ትዝታዎችን አስፍሯል፡፡

ደራሲው አክሎም ስንጨፍር በደንብ ግጥም ማውረድ በማይችል ልጅ ቅር የተሰኘ ቤተሰብ ከእኛው ጨዋታ የሚገለልበት ወቅትም ነበር፡፡

“ሆያ ሆዬ ጉዴ ብሯን ብሯን ይላል ሆዴ”  ሲል እና እኛ ስንቀበል… “ኧረ ብሯን ብሯን አለ ሆድህ” ይሉናል፡፡ “ሆያ ሆዬ ናና ልምጣ ወይ ወደ ማታ” ስንል ደግሞ “አሁን ገና አዋቃችሁልኝ ማታ ኑ” ይሉናል በማለት የቡሄ ሰሞን ትዝታን በዘመን ተሻጋሪ መጽሐፉ ከትቦታል፡፡ አዲስ አበባ ተወልደው ክፍለ ሀገር ያደጉ ይመስል የግጥም አወራረዱን አሳምረው የሚያውቁ ጓደኞችም ነበሩኝ ይላል ደራሲው፡፡

ሆያ ሆዬ ሆ

የኔማ እመቤት ሆ

የፈተለችው ሆ

የሸረሪት ድር ሆ

አስመሰለችው

…ሆያ ሆዬ ናና

በሰፊው ጎዳና… ዘነበ በልጅነት ውሻ ግቢ ያለበት ቤት ገብቶ ሆያ ሆዬ መጨፈሩን፣ ሽልማት ገንዘብ ተቀብሎ ወደ ቤት መመለስ የሚያስከትለውን ቁጣ፣ ልጆች በሆያ ሆዬ ወቅት የሚያሳዩት ባህሪን እና ከማህበረሰቡ ጋር የሚኖራቸውን መስተጋብር በሳቢ አተራረክ ከትቦታል፡፡

ሆያ ሆዬ ከመጽሐፍ ባለፈም በብዙ ሙዚቀኞች ተቀንቅኗል፡፡ በጥበብ ጅረት ውስጥም ከትውልድ ትውልድ ተላልፏል፡፡ ሆያ ሆዬን በሙዚቃ ከተጫወቱ ሰዎች ውስጥ ወጣቱ ቃልአብ ክንፈ ይጠቀሳል፡፡ “ቃልኪን” በሚል የመድረክ ስም የሚታወቀው ወጣቱ ድምጻዊ ሙዚቃውን የሰራው የዛሬ ሁለት ዓመት ነበር። እስኪ ከሙዚቃው ስንኞች ውስጥ ጥቂቶችን እንቀንጭብ…

መጣና በአመቱ

እረ እንደምን ሰነበቱ

ክፈት በለው ተነሳ

ይህን አንበሳ

ክፈት በለው በሩን

የጌታዬን

ሆያ ሆዬ ሆ

ሆያ ሆዬ ሆ

እዚህ ቤቶች እንደምን ናችሁ

በዓመት አንድ ቀን መጣንላችሁ

በዓመት አንድ ጊዜ ለመጣ እንግዳ

ምሳው ሙክት ነው እራቱ ፍሪዳ

ሆያ ሆዬ ጉዴ

ጨዋታ ነው ልማዴ፡፡ በማለት ነሃሴ ወር እና ሆያ ሆዬ በዓመት አንድ ጊዜ የሚመጡ፣ ተናፋቂና ተወዳጅ ወቅት መሆናቸውን አቀንቅኗል፡፡

በአጠቃላይ ሆያ ሆዬ የብዙ ሰዎች ትዝታ እና የህጻናት ፌሽታ ነው፡፡ ወቅቱ በተለያዩ መጽሐፍት፣ ግጥሞች፣ ዘፈኖችና ለሌሎች የኪነ ጥበብ ስራዎች መነሻ ሃሳብ በመሆንም ያገለግላል፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review