ቢሊየነሩ ፓትሪስ ሞትሴፔ በድጋሚ የካፍ ፕሬዚደንት ሆነው እንደሚመረጡ ይጠበቃል

You are currently viewing ቢሊየነሩ ፓትሪስ ሞትሴፔ በድጋሚ የካፍ ፕሬዚደንት ሆነው እንደሚመረጡ ይጠበቃል

AMN – መጋቢት 2/2017 ዓ.ም

የካፍ መደበኛ ያልሆነው 14ኛው ጉባዔ ትናንት በግብጽ ካይሮ ተጀምሯል፡፡

ጉባዔው በዞናል ውይይት የተጀመረ ሲሆን፣ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማህበር ከካፍ ፕሬዚደንት ፓትሪስ ሞትሴፔ (ዶ/ር) ከስራ አስፈጻሚ አባላት ጋር ትናንት ተወያይተዋል፡፡

ዛሬም ከሌሎች ዞኖች ጋር የተናጠል ውይይቶች እየተደረጉ ነው፡፡

በነገው ዕለትም ዋናው ጉባዔ የሚደረግ ሲሆን፣ ለመጪው አራት ዓመታት ኮንፌዴሬሽኑን በስራ አስፈጻሚነት የሚመሩ ባለሙያዎች እንደሚመረጡ ይጠበቃል፡፡

በከፍተኛ ሙስና ተጠርጥረው ከኃላፊነት የተነሱትን ማዳጋስካራዊው አህማድ አህማድን ተክተው በፈረንጆቹ 2021 የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ሆነው የተመረጡት ደቡብ አፍሪካዊው የማዕድን ቢሊየነር ፓትሪስ ሞትሴፔ (ዶ/ር) በድጋሚ ለመመረጥ ቀዳሚ ትኩረት አግኝተዋል፡፡

እንደ ፎርብስ ሪፖርት ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ሀብት ያላቸው እና የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ቢሊየነር የሆኑት ሞትሴፔ ራሳቸውን ከእጩነት አግልለው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የደቡብ አፍሪካ ዞን እግር ኳስ ማህበር ባሳደረው ጫና ምክንያት ውሳኔያቸውን ሽረው በእጩነት መቅረባቸውን የሬውተርስ ዘገባ አስታውሷል፡፡

የማሜሎዲ ሰንዳውንስ እግር ኳስ ክለብ ባለቤት የሆኑት እና ከዓለም ዓቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ (ፊፋ) ፕሬዚደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ጋር ባላቸው የቀረበ ወዳጅነት የሚታወቁት ዶክተር ፓትሪስ ሞትሴፔ ለመጪዎቹ አራት ዓመታት ካፍን በድጋሜ እንደሚመሩ ይጠበቃል፡፡

ፓትሪስ ሞትሴፔ ካፍ ከተመሰረተበት 1956 ጀምሮ ሰባተኛው ፕሬዚደንት ናቸው፡፡

በነገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ የፓትሪስ ሞትሴፔ ተፎካካሪ ሌላ እጩ ስለመኖርና አለመኖሩ ዓለም ዓቀፍ መገናኘ ብዙሃን ያሉት ነገር የለም፡፡

ከፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ባሻገር የስራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫም ይጠበቃል፡፡

የካሜሮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንትና የባርሴሎና የቀድሞ አጥቂ ሳሙኤል ኢቶ ለካፍ ስራ አስፈጻሚነት እንደሚወዳደር ይታወቃል፡፡

እየተካሄደ ባለው 14ኛው የካፍ ጉባዔ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት አቶ ኢሳያስ ጂራ እና ምክትላቸው ዶክተር ዳኛቸው ንግሩ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እየተሳተፉ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review