የማይክሮሶፍት መስራች እና ባለቤት ቢል ጌትስ፣ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ለልገሳ ካዘጋጁት 200 ቢሊየን ዶላር ሀብታቸው፣ አብዛኛውን ለአፍሪካ ሀገራት የጤና እና ትምህርት ማሻሻያ አገልግሎት እንዲውል ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
ቢል ጌትስ ይህን ዕቅዳቸውን ይፋ ያደረጉት በአዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት ነው።
የጤና ሥርዓት እና ትምህርትን በማሻሻል፣ የሰዎችን እምቅ አቅም በማሳየት የአፍሪካ ሀገራት ወደ ብልጽግና እንዲያመሩ ማድረግ እንደሚቻል ቢል ጌትስ አመላክተዋል።
የአህጉሪቱ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችም፣ የጤና አጠባበቅ ሥርዓትን ለማሻሻል ሰው ሰራሽ አስተውሎትን እንዴት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ሊያስቡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የ69 ዓመቱ ባለፀጋ ቢል ጌትስ፣ እስከ ፈረንጆቹ 2045 የሀብታቸውን 99 በመቶ ለልገሳ እንደሚያውሉ ባለፈው ወር ማሳወቃቸው ይታወሳል።
በሀብት መጠናቸው በዓለም አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ቢል ጌትስ፣ የሀብታቸውን 99 በመቶ ቢለግሱም፣ አሁንም ቢሊየነር ከመሆን እንደማያግዳቸው ብሉምበርግን ጠቅሶ አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡