AMN – መጋቢት 4/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በከተማው ምንም ዓይነት የነዳጅ አቅርቦትም ሆነ ስርጭት እጥረት እንደሌለ ገልፆ፣ የነዳጅ ስርጭትን በሚያስተጓጉሉ ማደያዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ አስታውቀዋል፡፡
በከተማዋ የሚያስፈልገው የቤንዚን መጠን 1.4 ሚሊየን ናፍጣ ደግሞ እስከ 2 ሚሊየን መሆኑን ያስታወሡት የቢሮው ኃላፊ፣ በዛሬው ዕለትም በከተማዋ አገልግሎት በሚሰጡ ማደያዎች 3.01 ሚሊየን ሊትር ቤንዚን እና 3.87 ሚሊየን ሊትር ናፍጣ መቅረቡን ገልጸዋል።
ነገር ግን ከዚህ እውነታ በተጻራሪው አገልግሎት በማዘግየት እና ነዳጅ እያላቸው የለም በማለት እንግልት የሚፈጥሩ እና ህገ-ወጥ የሆነ ተግባር ውስጥ የገቡ ማደያዎች ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ነው ያስጠነቀቁት፡፡
ማደያዎች ከዚህ ህገ-ወጥ ተግባር እንዲቆጠቡ እና አገልግሎታቸውን እንዲያስተካክሉም አሳስበዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የነዳጅ ተጠቃሚዎችም በንግድ ቢሮ የ ፌስ ቡክ ገጽ (Addis Ababa Trade bureau) ላይ በየማደያው ያለውን የአቅርቦት መጠን መመልከት እና ህገ-ወጥ ድርጊቶችን መጠቆም የሚችሉ መሆኑን መግለፃቸውን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።