AMN – የካቲት 25/2017 ዓ.ም
ባህርዳር ሰላማዊ ከመሆኗ በላይ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የከተማዋን ዕድገት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በባህርዳር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማትና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝታቸውን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የመጀመሪያ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ የከተማዋን ውበት ከፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የጣና ዳርቻን ለህዝብ ክፍት የማድረግና ከዋና ዋና የከተማዋ መንገዶች ጋር የማገናኘት ሥራዎች፣ ሰፋፊ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችም በጥራት በመገንባት ላይ መሆናቸውን ተመልክተናል ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ የመብራት ስማርት ፖሎችን ጨምሮ ግብዓቶች በክልሉ በሚገኙ ፋብሪካዎች የሚመረት መሆኑም ትልቅ አቅም ፈጥሯል ነው ያሉት።
የባህርዳር የኮሪደር ልማት አጠቃላይ 22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ገልጸው፤ በዚህም በመጀመሪያው ምዕራፍ 3 ኪሎ ሜትር በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
አጠቃላይ የልማት ሥራው በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ለህዝብ ክፍት እንደሚሆን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ በቅርቡም ሁለተኛው ምዕራፍ እንደሚጀመር አንስተዋል።
ለከተማዋ ትልቅ ውበትና የገቢ ምንጭ የሚሆነው የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታም በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
ስታዲየሙ የፊፋና የካፍን መመዘኛዎች በማሟላት የወንበር ገጠማ ስራው በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን የሳር ተከላና ሌሎች መሰረተ ልማቶችም በመሟላት ላይ ናቸው ብለዋል።
ስታዲየሙ ዙሪያውን ውብ ገጽታ እንዲኖረው መደረጉን አድንቀው፤ በዚህ ዓመት ተጠናቅቆ ጨዋታዎችን እንዲያስተናግድ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከተማዋ ሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብርም አበረታች ጉዞ ላይ ናት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዘርፉ በርካታ የተማሩ ወጣቶች መሰማራታቸው ለውጤታማነቱ ትልቅ አቅም መሆኑን ገልጸዋል።
በሰንጋ ማድለብ፣ በወተት ምርት፣ በዶሮና እንቁላል እንዲሁም በአሳና አትክልትና ፍራፍሬ የተቀናጀ የሌማት ትሩፋት እየተካሄደ ሲሆን ይህም ስርዓተ ምግብን ለማሻሻል ወሳኝ ነው ብለዋል።
የልማት ስራዎች ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እንደተፈጠረባቸው ገልጸዋል።
ከተማዋ ሰላማዊ ድባብ የሚታይባት፣ ጎብኝዎች በስፋት የሚንቀሳቀሱባት ሆና ዘርፈ ብዙ የልማትና ኢንቨስትመንት ስራዎች እየተሳለጡ ይገኛሉ ያሉት አቶ ተመስገን፤ እነሱም የከተማዋን ዕድገት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸዋል ሲል የኢዜአ ዘግቧል።