በካፍ ኮንፌዴሬሽ ካፕ ኢትዮጵያን የወከለው ባህር ዳር ከነማ የቱኒዝያውን ክለብ አፍሪካንን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው 2ኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ የጣና ሞገዶቹን ሁለት የድል ግቦች አጥቂው ሀብታሙ ታደሰ በ58ኛው እና 90ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል፡፡
በጨዋታው ባህር ዳር ከነማዎች ኳስን መስርተው ለመጫወት ጥረት ያደረጉ ሲሆን ያገኟቸውን አጋጣሚዎችም ወደግብ በመቀየር አሸንፈው ለመውጣት ችለዋል፡፡
ክለብ አፍሪካን በአንጻሩ በረጃጅምና በቆሙ ኳሶች ግብ ለማግባት ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመሩት የጣና ሞገዶቹ በማጥቃቱና በመከላከሉ ጥሩ ሆነው ባመሹበት ጨዋታ ወደ ምድብ ድልድሉ ለማለፍ ዘጠና ደቂቃ ብቻ ይቀራቸዋል፡፡
ከካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ቀጥሎ ሁለተኛው ትልቅ ውድድር በሆነው መድረክ ቀሪውን የዘጠና ደቂቃ ጨዋታ የሚያሸንፉ ከሆነ ወይም አቻ አሊያም አንድ ለባዶ መሸነፍ 16ቱ የምድብ ድልድል ውስጥ ለመግባት ያስችላቸዋል፡፡
የጣና ሞገዶቹ በመድረኩ የመጀመሪያ ተሳትፏቸው ጥሩ እንቅስቃሴ እያሳዩ ይገኛሉ፡፡
በሙሉቀን ጌትነት
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!
YouTube ➲ http://bit.ly/3itThRr
Telegram ➲ http://bit.ly/3W4puw9
Facebook ➲ https://bit.ly/3CJVgI8
Twitter ➲ http://bit.ly/3IKQ3TZ