ባለስልጣኑ በማህበራዊ ሚዲያ የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰበ

You are currently viewing ባለስልጣኑ በማህበራዊ ሚዲያ የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰበ

AMN – ጥቅምት 11/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በግንባታ እቃ እና በእግረኛ መንገድ ላይ በራሷና በህብረተሰቡ ላይ ለትራፊክ አደጋ በሚያጋልጥ መልኩ ልመና ላይ የነበረች ግለሰብ ከስፍራው ለማስነሳት የተደረገው የደንብ ማስከበር ስራን ኃላፊነት የጎደላቸው ጥቂት ግለሰቦች በተሳሳተ መንገድ በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨታቸውን ባደረገው ክትትልና በህብረተሰቡ ጥቆማ ማረጋገጡን ገልጿል።

የተቋሙ ደንብ የማስከበር ተልዕኮ ለመወጣት በስራ ገበታዋ ላይ የነበረች የክትትል፣ ቁጥጥርና እርምጃ አወሳሰድ ኦፊሰር በልመና ላይ የነበረችውን ልጅ የያዘች ግለሰብ በስራ ስነ-ምግባር ዝቅ ብላ በማግባባት ቦታው ለራሷ፣ ለልጇና ለህብረተሰቡ አደጋ የሚፈጥር መሆኑን በመግለፅ ከስፍራው እንድትነሳ መጠየቋ ተመላክቷል።

ግለሰቧም ድርጊቷ በራሷ፣ በልጇ እና በህብረተሰቡ ላይ አደጋ የሚፈጥር መሆኑን ተገንዝባ ከስፍራው የተነሳች ሆኖ ሳለ ኃላፊነት የጎደላቸው ጥቂት ግለሰቦች የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ጭምር የራሳቸውን ስልክ ቁጥር ማስቀመጣቸው እና መረጃውን በተሳሳተ መልኩ ማሰራጨታቸው ባለስልጣኑ ባደረገው ክትትል የተመለከተ መሆኑን ገልጿል፡፡

ግለሰቦቹን መረጃውን በማጠናከር በህግ ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን ባለስልጣን መስርያ ቤቱ አስታውቋል።

ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ የተሳሳተ መረጃ ከሚያሰራጩ አካላት ባለማወቅ ከመተባበር እራሱን እንዲጠብቅ በመግለፅ የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋል።

በቦታው ደንብ ስታስከብር የነበረችው ኦፊሰር ግለሰቧን በስራ ስነ-ምግባር በማግባባት ዝቅ ብላ እንድትነሳ የጠየቀች መሆኑና በመግባባት በአካባቢው ከተገኙ ህብረተሰብ ድጋፍ እንደተደረገላት ከስፍራው ከነበሩ ሰዎች እና በፎቶ ማስረጃ መረጋገጡን ከአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review