AMN- ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም
በ2017 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 533 ሺህ ሰዎች አንድነት ፓርክን፣ ወዳጅነት ፓርክ ቁጥር አንድና ሁለት እንዲሁም ሳይንስ ሙዚየምን መጎብኘታቸው ተገለጸ።
እንደ አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ ገለፃ፤ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎቹ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ከተደረጉበት ጊዜ ጀምሮ የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ተስፋዬ አሻግሬ በአንድነት ፓርክ የመካነ እንስሳትና አኳርየም ዳይሬክተር ሲሆኑ፤ በፓርኩ ለ620 የዱር እንስሳት እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ከእነዚህም መካከል ወፎች፣ የውቅያኖስ ዓሳ ዝርያዎች፣ ሥጋ በልና ሳር በል እንስሳት እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ከውጭ አገራትም ሆነ ከሀገር ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኚ ወደ ፓርኩ እንደሚመጣ ጠቁመዋል።
በዚህም የሀገር ውስጥ ጎብኚው ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን አንስተው፤ እንደዚህ ዓይነት ፓርክ የአገር ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
በተለይም በመካነ እንስሳት ዘርፍ ላይ ብዙም እንዳልተሰራበትና በቀጣይ የሚሰራበት ቢሆን ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ከፍ እንደሚያደርገው አስተያየታቸውን አክለዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ስኡድ አብደላ በወዳጅነት ፓርክ በሚገኘው የአምሮኝ ችክን ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ፤ ወደ ሥፍራው የሚመጣ የጎብኚ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
ከውጭ አገር ለሚመጡ ጎብኚዎች ደግመው እንዲመጡና ሌሎች ሰዎችንም ለጉብኝት እንዲጋብዙ ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ በመስጠት የድርሻችንን እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል።
አክለውም መሰል የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን በሌሎች ቦታዎችም በማስፋፋት ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ መሻሻል አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ሊሰራበት ይገባል ነው ያሉት።
የአንድነት ፓርክ ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ጌታቸው በየነ በበኩላቸው፤ የጉብኝት ሥፍራዎች ከተማ ውስጥ ብዙም ስላልነበሩ የጉብኝት ባህላችን ብዙም እንዳልነበር ገልፀዋል።
ነገር ግን በአዲስ አበባ በቅርቡ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች የሕዝቡን የመጎብኘት ባህሉ እንዲዳብር ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከቱ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህንንም ተከትሎ አንድነት ፓርክን ጨምሮ በአንድነት ፓርክ ሥር በሚተዳደሩት ወዳጅነት ፓርክ ቁጥር አንድና ሁለት እንዲሁም ሳይንስ ሙዚየም በ2017 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 533 ሺህ ሰዎች መጎብኘታቸውን አንስተዋል።
ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት የአገር ውስጥ ጎብኚዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአንድነት ፓርክ ሊጎበኙ የሚችሉ በርካታ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መስህቦች፣ የተለያዩ የዱር እንስሳት፣ ሙዚየሞች ስላሉ ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የአገር ውስጥና የውጭ ዜጎች ጎብኝተው እንዲመለሱም ጥሪ ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡