ባለፉት ስድስት ወራት ከ2 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል – የስራና ክህሎት ሚኒስቴር

AMN – ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም

ባለፉት ስድስት ወራት ከ2 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እንደገለፁት ባለፉት ስድስት ወራት ከክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ከአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነት አኳያ አበረታች ተግባር ተከናውኗል።

በሀገር ውስጥ፣ በውጭ ሀገር እና በሌሎች አማራጮች ዜጎችን በቋሚነት የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የተሰራው ስራ አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ2 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም ለ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች በሀገር ውስጥ እንዲሁም 300ሺህ የሚሆኑት በውጭ ሀገር ቋሚ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭ የዲጂታል ክህሎት በማሳደግ ለስራ ዕድል ፈጠራ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የስራ ዕድል ፈጠራው በቀጣይ ወራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።

ሚኒስቴሩ በ2017 በጀት አመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review