- ከ375 ሺህ በላይ አባወራዎችና እማወራዎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ታቅፈው ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባሉት ዓመታት በኢትዮጵያ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተለያዩ መስኮች የሚታዩና ተጨባጭ የሆኑ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም እንደ ትምህርትና ጤና ባሉ የማህበራዊ ልማት ዘርፎች የተሰሩት ይጠቀሳሉ፡፡ ብልፅግና ፓርቲ ከጥር 23 እስከ ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም ለሦስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ሲያጠናቅቅ ባወጣው የአቋም መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ አካታችና ውጤታማ የማኅበራዊ ልማት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጿል፡፡ በተለይ በጤናው ዘርፍ በሽታን ቀድሞ የመከላከልና አክሞ ማዳን ፖሊሲን በመከተል ጤናማና አምራች ትውልድ ለመፍጠር የሚያስችሉ ስኬታማ ስራዎች እንደተሰሩ ተነስቷል፡፡
በጤናው ዘርፍ ውጤታማ ስራዎችን በመከወን የኢትዮጵያውያን መዲናና የአፍሪካውያን መናኸሪያ የሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ተጠቃሽ ናት። ከተማዋ ባለፉት ዓመታት የዘርፉን ፍትሀዊ ተደራሽነትና አገልግሎት አሰጣጥ ለማረጋገጥ ሰፋፊ ስራዎች ያከናወነች ሲሆን የሚከተሉትን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል፡፡
የጤና ተቋማት ግንባታ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በአሁኑ ወቅት ሰባት ሆስፒታሎችና 97 የጤና ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጤና ተቋማትን አቅም ለማሳደግ የነባርና አዳዲስ የጤና ተቋማት ግንባታ ስራዎች በሰፊው ተሰርተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሀንጋቱ መሀመድ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ ሆስፒታሎች ረጅም ዓመት ዕድሜ ያስቆጠሩ፣ ያረጁና በመሀል የከተማዋ አካባቢ ተከማችተው የሚገኙ ናቸው፡፡
በእነዚህ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት የሚያገኙ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ ፍላጎቱን ለማስተናገድም ሰፋፊ የማስፋፊያ እና አዳዲስ የጤና ተቋማት ግንባታ ስራዎች ተሰርተዋል፤ በመሰራት ላይም ይገኛሉ፡፡
ለማሳያነትም በዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባለ አራት ወለል ዘመናዊ የዓይን ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታልም ባለ አምስት ወለል ዘመናዊ ህንጻ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ከሰሞኑ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የሰጡት መረጃ ያሳያል፡፡
በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ከነባሩ ሆስፒታል የበለጠ 350 አልጋዎች ያሉት ባለ ስምንት ወለል ህንፃ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ በዚያው ሆስፒታል ተዘግቶ የነበረ የዓይን ህክምና ማዕከልም ተከፍቶ አገልግሎት እንዲሰጥ የተደረገው ከለውጡ ወዲህ ባሉት ዓመታት እንደሆነ ዶ/ር ዮሐንስ ያስረዳሉ።
የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታልም መጀመሪያ ሲገነባ የእናቶችና ህጻናት ህክምና አገልግሎት ለመስጠት ቢሆንም ሁሉንም አገልግሎቶች መስጠት እንዲችል ተደርጓል፡፡ አገልግሎቱን ለማሳደግ በአሁኑ ወቅት ባለ ስድስት ወለል ከ300 አልጋዎች በላይ ያሉት ህንጻ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡
ከለውጡ ዓመታት በፊት ለእናቶች የወሊድ ህክምና አገልግሎት በማቅረብ ረገድ የፍትሐዊ ተደራሽነት ችግር እንደነበር ያነሱት ወ/ሮ ሀንጋቱ በበኩላቸው፣ 400 አልጋዎች ያሉት የአበበች ጎበና የእናቶችና ህጻናት ሆስፒታል ከተከፈተ በኋላ እናቶች ወረፋ እየጠበቁ የሚወልዱበትን ሁኔታ ማስቀረት ተችሏል፡፡
ከዚህ ባሻገር የጤና ፍትሐዊነትን ለማስፈን ሁለት ትላልቅ፣ ዘመናዊ፣ ከነባር ሆስፒታሎች የተሻለ አቅም ያላቸው ሆስፒታሎች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል። በኮልፌ ቀራኒዮ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የሚገኙትና በመጠናቀቅ ላይ ያሉት ሆስፒታሎቹ እያንዳንዳቸው ከ450 በላይ ሰዎችን አስተኝቶ ማከም የሚያስችል አቅም አላቸው፡፡
በጤና ጣቢያ ረገድ አንዳንዶቹ አነስተኛ የማህበረሰብ ክፍልን ታሳቢ አድርገው የተሰሩና ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ እንደመሆናቸው፤ አሁን ያለውን ፍላጎት ለመሙላት በ28 ጤና ጣቢያዎች የማስፋፊያ ግንባታ ተከናውኗል፡፡ አራት የአዳዲስ ጤና ጣቢያዎች ግንባታም በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ 19 ጤና ጣቢያዎች ለእናቶች የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ተደርጓል፡፡ በዚህም እናቶች ያለምንም ክፍያ በነፃ ህክምና የሚያገኙ ሲሆን ይህም የጤና አገልግሎት ፍትሐዊነትና ተደራሽነትን ማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ ወይዘሮ ሀንጋቱ ተናግረዋል፡፡
በጤናው ዘርፍ ከለወጡ በፊት ከነበረው አኳያ አሁን ላይ በተለያዩ አገልግሎቶች ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ተችሏል፡፡ ለማሳያነትም በጤና ተቋማት ከለውጡ ዓመታት በፊት የተመላላሽ ህክምና ከነበረበት 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን 14 ሚሊዮን፣ የአስተኝቶ ማከም ከ150 ሺህ ወደ 225 ሺህ፣ የወሊድ አገልግሎት ከ140 ሺህ ወደ 190 ሺህ፣ የቀዶ ህክምና አገልግሎት የሚሹ ታካሚዎች ከ38 ሺህ ወደ 95 ሺህ፣ የደም ግፊት ልየታ ከ230 ሺህ ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን፣ የስኳር መጠን ልየታ ከነበረበት 52 ሺህ 462 ወደ 228 ሺህ ማሳደግ እንደተቻለ አንስተዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ የአስተኝቶ ህክምና ምጣኔን፣ የእናቶችን፣ የህጻናትን እና የድንገተኛ ታካሚዎችን ሞት በመቀነስ የዓለም ጤና ድርጅት ከሰሃራ በታች ያሉ ሃገራት በፈረንጆቹ 2030 በጤናው ዘርፍ እንዲያሳኩት ከያዘው ጊዜ አስቀድማ ማሳካት እንደቻለች ወይዘሮ ሃንጋቱ ተናግረዋል፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን
በጤናው ዘርፍ የተሰራውና በተጨባጭም ውጤት የተገኘበት የህክምና አገልግሎት ለማግኘት አቅም የሚያንሳቸው ዜጎች በአነስተኛ መዋጮ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችለው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ነው፡፡ አገልግሎቱ በአዲስ አበባ ከተማ በ2010 ዓ.ም በአስር ክፍለ ከተሞች በሚገኙ አስር ወረዳዎች ላይ ከ15 ሺህ በላይ አባወራዎችና እማወራዎችን በማቀፍ ነበር የጀመረው፡፡ በየዓመቱም ህብረተሰቡ ጥቅሙን እየተረዳ፣ ተደራሽነቱም እያደገ መጥቷል፡፡ አሁን ላይ ከ375 ሺህ በላይ አባወራዎችና እማወራዎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ታቅፈው ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ይህም ፍትሐዊነትን ማስፈን ያስቻለ ትልቅ እምርታ እንደሆነ በኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የአዲስ አበባ ክላስተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አይካ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡
አንድ ቤተሰብ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ታቅፎ የጤና አገልግሎት ለማግኘት መክፈል ያለበትና በጥናት የተለየው ዓመታዊ ወጪ 2 ሺህ ብር ቢሆንም፤ አባላቱ በዓመት 1 ሺህ 500 ብር በመክፈል ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ። ከዚህ ውስጥ የቀረውን 500 ብር የከተማ አስተዳደሩ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ እየከፈለ ነው፡፡ በተጨማሪም የመክፈል አቅም የሌላቸው 119 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን የክፍያ መዋጮ በመሸፈን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡
ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ሀንጋቱ እንደገለፁት፣ የከተማ አስተዳደሩ ለማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚዎች የህክምና አገልግሎት በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ብር ድጎማ ያደርጋል፡፡ በዚህም የዜጎችን የጤና ወጪ ጫና በመቀነስ፣ የጤና አገልግሎት ሽፋንን በማሳደግ፣ በገንዘብ እጦት ምክንያት ህክምና የማያገኙ ዜጎችን ህክምና እንዲያገኙ በማስቻል ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አክለው ገልጸዋል፡፡
ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ትግበራ
ሌላው በጤናው ዘርፍ አካታችነትን ለማረጋገጥ በትኩረት የተሰራበትና ውጤት የተገኘበት የከተማ ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ትግበራ ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም ቤተሰብንና ማህበረሰብን ማዕከል አድርጎ ጤናን የማበልጸግና በሽታን መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠጣል፡፡
በጤና ባለሙያዎች አማካኝነት በጤና ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤት፣ ቤት ለቤት፣ በስራ ቦታዎችና የጎዳና ተዳዳሪዎችን ጨምሮ ህብረተሰቡ ጤናውን እንዲጠብቅ የማስተማር እንዲሁም በተመረጡ ቦታዎች የኤች አይ ቪ፣ ቲቢ፣ የደም ግፊት፣ ስኳርና ካንሰር ህመሞች ምርመራ በማድረግና በመለየት፣ የተጠረጠሩ ሰዎች ወደ ህክምና ተቋም እንዲሄዱና ህክምና እንዲያገኙ ክትትል ይደረጋል፡፡ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ንጽህና እንዲጠብቅ፣ ራሱን ከበሽታ እንዲከላከል ንቃተ ህሊናውን በማሳደግ የጤና ጉዳትንና ሞትን መቀነስ እንደተቻለ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የከተማ ጤና ኤክስቴንሽንና መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ቡድን መሪ አቶ ፍቅሮም ገብረ መድህን ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የጎዳና ተዳዳሪዎች ትኩረት አይሰጣቸውም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት እነሱንም በማካተት የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ በጤና ተቋም እንዲወልዱ፣ ልጆቻቸው ክትባት የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር የጤና አገልግሎቱ ፍትሐዊና አካታች እንዲሆን እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ቀዳማይ ልጅነት መርሀ ግብር
ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የጤና አገልግሎትን ከማቅረብ አኳያ አካል ጉዳተኞችን፣ አረጋዊያንን፣ እናቶችን እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን ትውልድ ጭምር ያገናዘበ የጤና አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ወይዘሮ ሃንጋቱ ያነሳሉ፡፡ ለዚህም ህጻናት በሁለንተናዊ መልኩ ተገቢውን እድገት እንዲያገኙና ለሀገር የሚጠበቅባቸውን አበርክቶ እንዲወጡ ለማስቻል የተነደፈው የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ተጠቃሽ ነው፡፡ ቀዳማይ ልጅነት ህፃናት ከእናታቸው ማህፀን ካሉበት እስከ 6 ዓመት ያለውን የህፃናት የዕድገት ሂደት የሚመለከት ሲሆን፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚደረግላቸው እንክብካቤ አካላዊና አእምሯዊ እድገታቸው ላይ ወሳኝነት አለው፡፡
በከተማ ደረጃ በተደረገ ጥናት እስከ 6 ዓመት ካሉት ህጻናት ውስጥ 13 በመቶ የሚሆኑት ከእድሜያቸው አኳያ የሚጠበቅባቸውን የእድገት ሂደት ጠብቀው እያደጉ እንዳልሆነ ያሳያል። ታዲያ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀዳማይ ልጅነት መርሀ ግብርን በመጀመር ጤናና አምራች ትውልድ ለማፍራት እየሰራ ይገኛል፡፡
ወይዘሮ ሃንጋቱ እንደገለፁት፣ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2026 አዲስ አበባን ከአፍሪካ ልጆችን ለማሳደግ ተመራጭ የሆነች ከተማ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ ለዚህም ከጽንስ ጀምሮ ህፃናት ተገቢውን እንክብካቤ አግኝተው እንዲያድጉ ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ ድጋፍ የሚያደርጉ ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ የቤት ለቤት የወላጅና ልጆች ምክር ሰጪ ባለሙያዎችን በማሰልጠን እንዲሰማሩ ተደርጓል፡፡
ከዚህ ባሻገር በከተማዋ ምቹ የእግረኛ፣ የሳይክል መንገዶች፣ አረንጓዴ ስፍራዎችን በማካተት የተሰራው እና በመሰራት ላይ ያለው የኮሪደር ልማት ሌላው ህብረተሰቡ ጤናው የተጠበቀና አምራች እንዲሆን የሚያስችል ነው፡፡ ዶክተር ዮሐንስ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እንደገለፁት፣ አንድ ሰው ጤናውን ለመጠበቅ በቀን ለ30 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ምቹ የእግረኛ እና የሳይክል መንገዶች መኖራቸው ህብረተሰቡ በእግሩ እየተዝናና ጤናውን የሚጠብቅበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የጤና አገልግሎቱን አካታች፣ ፍትሐዊና ተደራሽ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በቀጣይም ሁሉም ዜጋ የጤና አገልግሎት ማግኘት እንዲችል አካታችነቱንና ጥራቱን እያሰፉ መሄድ ያስፈልጋል እንላለን፡፡
በስንታየሁ ምትኩ