የ2017 በጀት ዓመት የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸም እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል።
በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የማክሮ ኢኮኖሚና የዘርፎች አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
የሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት፣ የዘርፎች ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ማጠናከር፣ የኢንቨስትመንት ንግድን ከባቢ ማሳደግ እንዲሁም የመንግስት የመፈጸም አቅምን ማጎልበት ዓላማ አድርጎ ወደ ትግበራ መግባቱን አብራርተዋል።
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በአራቱም ምሶሶዎች የተሻለ ስኬት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ ይህም የስምንት ነጥብ አራት በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማስዝገብ የተያዘው እቅድ እንደሚሳካ ያመላከተ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በበጀት ዓመቱ ኢንቨስትመንትና ቁጠባ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ያላቸው ድርሻ መሻሻሉንም ነው የጠቀሱት።
ኢንቨስትመንት ከሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት አኳያ ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት 20 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉን አንስተዋል።