ባለ ራዕይ አመራር መኖሩን ያሳየው የኢኮኖሚ እምርታ

You are currently viewing ባለ ራዕይ አመራር መኖሩን ያሳየው የኢኮኖሚ እምርታ
  • Post category:ልማት

ከኒው ዮርክና ጀኔቫ በመቀጠል ሦስተኛዋ የዓለም የዲፕሎማሲ ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ ባለፉት የለውጥ ዓመታ በኢኮኖሚው መስክ በርካታ ውጤቶችን አስመዝግባለች፡፡ በዚህም የከተማዋን ውበትና ገፅታ የቀየሩና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ያሳደጉ በርካታ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

ገጽታዋን ከቀየሩ ትላልቅ የልማት ስራዎች መካከል ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆኑት የአንድነትና እንጦጦ ፓርኮች፣ ወዳጅነት አደባባይ እና የሳይንስ ሙዚየም ይጠቀሳሉ።

እነዚህ የልማት ስራዎች ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠራቸው ባሻገር የአዲስ አበባን ተወዳዳሪነት ያሳደጉ የልማት ስራዎች ናቸው፡፡

ባለፉት ዓመታት በከተማዋ እውን ከሆኑ እነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል የዓድዋ ድል መታሰቢያ ተጠቃሽ ነው፡፡ መታሰቢያው የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴውን በማነቃቃትና ማህበራዊ መስተጋብርን በማጠናከር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አስገኝቷል፡፡

በውስጡ ብዙ ታሪኮችን የያዘ በመሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች የሚጎበኙት፣ የኢትዮጵያ ገጽታ የሚገነባበትና ገቢ የሚገኝበት የቱሪስት መስህብ ስፍራ ሆኗል፡፡

በመታሰቢያው በሚገኙ የተለያዩ ክፍሎች እየተደረጉ ያሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ለከተማዋ ምጣኔ ሀብት ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው ተብሎ ይታመናል፡፡

ትላልቅ የስብሰባ አዳራሾች፣ የኤግዚቢሽን ማዕከላት፣ ሲኒማ ቤቶች ከዚህ በፊት እንደ ሚሊኒዬም አዳራሽ፣ ኤግዚቢሽን ማዕከልና ሌሎች የስብሰባ ማዕከላት ይደረጉ የነበሩ ኹነቶችን በተሻለ ጥራት ለማስተናገድ የተመቹ በመሆናቸው በኪራይ ብዙ ገቢ ማመንጨት አስችለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር መታሰቢያው በከተማዋ ማዕከላዊ አካባቢ የተሰራ በመሆኑ በተለያዩ ርቀት የሚኖሩ ነዋሪዎች በትርፍ ጊዜያቸው ወደ አካባቢው በመምጣት የሚዝናኑበትን ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ የውጭ ሀገር እንግዶችም መታሰቢያውን ሲጎበኙ የሚገኘው ገቢም የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመደገፍ ላይ ነው፡፡

ሌላዩ የልማት ስራ የኮሪደር ልማቱ ሲሆን ልማቱ የተሽከርካሪ እና እግረኛ መንገዶችን ፣ የአረንጓዴ ስፋራዎችን ሽፋን፣ የሳይክል መንገዶችን የማስፋት፣ የውሃ ፍሳሽና የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ደረጃ የማሳደግ፣ ህንፃዎች ተመሳሳይ ስታንዳርድ እንዲይዙ ማድረግን ያካተተ ነው። የኮሪደር ልማቱ በአዲስ አበባ ውበት፣ ጽዳትና ገፅታ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል፡፡
ይህም አዲስ አበባን የሚያማምሩ ጎዳናዎች ካላቸው ከተሞች ተርታ የሚያሰልፋት፣ ሰዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ፣ ብስክሌትን ጨምሮ ከአየር ብክለት ነፃ የሆኑ የትራንስፖርት መጓጓዣዎችን እንዲጠቀሙ ያስቻለ ብቻ ሳይሆን ውብና ፅዱ አካባቢ፣ ጤናማ ማህበረሰብ በመሳብ፣ ቱሪዝምን በማሳደግ ትልቅ ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳን እውን በማድረግ በኩል ሚናው የጎላ ነው፡፡

በሌላ በኩል እንደሚታወቀው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት እንዲሁም ለእነዚህ ችግሮች መባባስ ምክንያት የሆኑት ደላሎች ለህብረተሰቡ ምሬትና የኑሮ ጫና ዋንኞቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ ከማሳው የሚሸጥበት ዋጋ እና ምርቱ በከተሞች ለሸማቹ በሚቀርብበት ዋጋ መካከል ከፍተኛ ልዩነት ይታያል፡፡ በዚህም የተነሳ አምራቹና ሸማቹ እየተጎዳ ደላሎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት አካሄድ ነበር፡፡
ምርቶች ሸማቹጋ እስኪደርሱ ድረስ ያለውን የተንዛዛና እሴት የማይጨምር ይልቁንም ለዋጋ ንረት ምክንያት የሆነ የደላላ ጣልቃ ገብነት ለመከላከል፣ አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ በከተማዋ ዋና ዋና መግቢያ በሮች የግብርና ምርቶች ማከፋፈያና መሸጫ የገበያ ማዕከላት ተገንብተው ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 አያት፣ ወረዳ 5 ሰሚት እንዲሁም ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ቤተል የተገነቡ ግዙፍ ማዕከላት ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

እነዚህ የገበያ ማዕከላት የዋጋ ንረትን በማርገብ ትልቅ አስተዋፅኦ ያላቸው ሲሆን ከዓመታት በፊት በከተማዋ የነበረው የአትክልትና ፍራፍሬ መገበያያ ስፍራዎች ቁጥር በጣም አናሳና የከተማዋን ነዋሪዎች የማይመጥኑ ነበሩ። በቅርብ ዓመታት በተለያዩ የከተማዋ መግቢያና መውጫ በሮች የተገነቡ የገበያ ማዕከላት ለተጠቃሚው የግብርና ምርቶችን በየአካባቢው በወቅቱ ለማግኘት አስችለዋል፡፡ ሸማቹ ረጅም ርቀት ተንቀሳቅሶ የመጓጓዢያ ወጪ ተጨምሮበት በውድ ዋጋ የሚገዛበትን ሁኔታ በማስቀረት ምርቶቹን በአካባቢው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ አስችለዋል፡፡

የገበያ ማዕከላት ምርቶችን ከማቅረብ በተጨማሪም ለበርካታ ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ማህበረሰቡ ትኩስ ምርቶችን እንዲያገኝ እንዲሁም መንግስትም ስርዓቱን ጠብቆ ከሚካሄደው ግብይት ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ በኩል ትልቅ እገዛ አድርገዋል፡፡

በመዲናዋ ለሚገኙ የሸማች ህብረት ሥራ ማኅበራት የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦት በማመቻቸት የምርት አቅርቦትን በማሳለጥና የገበያ ተደራሽነትን በማረጋገጥ የሸማች እና ህብረት ስራ ማህበራት የኑሮ ውድነቱን በማቃለል ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የፋይናንስ አቅማቸውንም በማጎልበት ለከተማዋ የሚያቀርቡትን ምርት ለማሳደግ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ በማመቻቸት ሰፊ የሆነ የሰብል ምርቶችን እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡
በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች አምራችና ሸማቹ የሚገናኙባቸው የቅዳሜ እና የእሁድ ገበያዎችን በማቋቋም፣ ገበያዎቹ ከመደበኛው የገበያ ዋጋ ባነሰ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለነዋሪዎች እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡

እንደ ከተማ ስንመለከት በብዙ የዓለም ሀገራት ከተሞች የከተማ ግብርናን በመተግበር 20 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚሆነውን የምግብ አቅርቦታቸውን ይሸፍናሉ፡፡ ይህንን ተሞክሮ በመውሰድ በመዲናዋ በተለያዩ የጓሮ አትክልት፣ የስጋና እንቁላል ዶሮ፣ ወተትና ማር ምርቶች በልዩ ሁኔታ በማምረት ውጤታማ መሆን ተችሏል፡፡

የከተማ ግብርና የኑሮ ውድነትን ለማርገብ፣ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተስማማ ልማት ለማምጣት፣ የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ ትኩስና ጤናማ የግብርና ምርት ፍጆታዎችን ለማቅረብ ትልቅ አቅም ያለው በመሆኑ እንደነ ታይላንድ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና የመሳሰሉ የእስያ ሀገራት ከተሞች የምግብ ዋስትና ችግርን ለማቃለል ተጠቅመውበታል። ከዚህ አኳያ በአዲስ አበባም የተከናወኑ ስራዎች ፋይዳቸው ከፍ ያለና ሊበረታቱ የሚገቡ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል አዲስ አበባ ላይ የብዙ ጎስቋላ አካባቢዎች ገፅታ መቀየር ብቻ ሳይሆን የሰው ህይወትንም የመቀየር ስራ በስፋት ተከናውኗል፡፡ ከ700 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የምገባ ተጠቃሚ በማድረግ፣ ምንም ዓይነት አቅም የሌላቸው ዜጎች ምግብ በነፃ የሚመገቡባቸው የምገባ ማዕከላት በማስፋፋት፣ የበርካታ አቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ የተሰሩ ስራዎችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡

ሌላው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ህይወት ለማቃለል የተሰሩ ስራዎችን ስናነሳ የዳቦ ፋብሪካዎች ግንባታን አብሮ መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪ በየአካባቢው በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ የሚያገኝበትን ሁኔታ በመፍጠር የኑሮ ጫናን ለመቀነስ መንግስት ከግል ባለሀብቶች ጋር አጋርነት በመፍጠር በርካታ የዳቦ ፋብሪካዎችን ተገንብተዋል፡፡ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ባሉት ዓመታት በአዲስ አበባ በቀን እስከ 300 ሺህ ዳቦ ይመረት የነበረው ዛሬ ላይ በቀን በሚሊዮን የሚቆጠር ዳቦ ማምረት የሚቻልበት አቅም ተፈጥሯል፡፡

በሰለሞን በቀለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review