በጎነት ከሰብዓዊነት ከፍታ ላይ የሚያደርሰን ኃይል እንደሆነ በበጎነት ዙሪያ የተከተቡ ድርሳናት ያስነብባሉ፡፡ በጎ ስንሆን “ለሰው ልጅ ችግሮች ሁሉ መፍትሄው እኔ ነኝ” ወደሚል የትህትና ልዕልና ደረጃ እናድጋለንም ይላሉ፡፡ “በጎነት ለራስ ነው፤ በጎነት ለሀገር ነው። ሰው በጎ ሲሆን ለሌለው ይረዳል፣ የተከፋውን ያፅናናል፤ የታመመውን ይጠይቃል” ሲሉም ያትታሉ፡፡ ለመሆኑ መልካምነት በአዲስ አበባ ከተማ ምን መልክ አለው?
ወይዘሮ ዘይቱና አህመድ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ነዋሪ ናቸው፡፡ እርጅና ያጎሳቆለው ቤታቸው ህይወትን አክብዶባቸው መክረሙን ይናገራሉ፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የአልጋ ቁራኛ የሆነ ወንድማቸውን ለረጅም ዓመታት በዚሁ ቤት ውስጥ ለማስታመም መገደዳቸው ተጨማሪ ፈተና ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡ በክረምት የዝናብ ፍሳሽ እና ጎርፍ ማስገባቱ፤ መጸዳጃ ቤቱም ከማርጀቱ የተነሳ ቢያፀዱትም የማይፀዳ በመሆኑ የሚያመነጨው ሽታ፣ ነፍሳትና እርጥበት ለተጓዳኝ በሽታ ሲዳርጋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
“ቤታችን እንኳን ሰው ሊኖርበትና ልጅ ሊያድግበት ቀርቶ በአጠገቡ አልፎ ለመሄድም መንፈስን የሚያውክ ነበር” የሚሉት ወይዘሮ ዘይቱና፣ “ከሞቱት በላይ ካሉት በታች የሆነ ኑሮ እንኖር ነበር፡፡ ኑሮን ለማሸነፍ ወደ አረብ ሀገርም ሄጄ ነበር፡፡ ነገር ግን ወንድሜን ከማስታመም አልፎ ቤት የሚያድስልኝ ጥሪት ማፍራት አልቻልኩም” ይላሉ፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ነበር ያረጁና የተጎሳቆሉ ቤቶችን የማደስ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስተባባሪነት የተጀመረው፡፡ ወይዘሮ ዘይቱናም የዚህ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የወረዳው የበጎ ፈቃድና የህብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በአካባቢው የሚገኝ አንድ ባለሃብት በማስተባበር ቤታቸው እንዲታደስላቸው ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በስፍራው ተገኝቶ እንደታዘበው አሁን የወይዘሮ ዘይቱና ቤትና መፀዳጃ ቤቱ ታድሶ ለመኖሪያነት የተመቸ ሆኗል፡፡ ወይዘሮ አድሊ ጌታቸው በአዲስ ከተማ ከፍለ ከተማ የወረዳ 4 ነዋሪ ሲሆኑ አቅመ ደካማ እናት ናቸው፡፡ ችብስ በመጥበስ የእለት ጉርሳቸውን የሚሸፍኑ ሲሆን፣ ባለቤታቸውን በሞት ማጣታቸው የኑሮን አቀበት ለብቻቸው እንዲገፉ አስገድዷቸዋል። ቤታቸውም በእርጅና ዘምማ ዓመታትን ቆይታለች። በክረምት ዝናብ፣ ፍሳሽና ብርድ፤ በበጋ ደግሞ ጸሐይ ተፈራርቆባቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነውም ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ የዘመዶቻቸውን ሶስት ህጻናት ሰብስበው ያሳድጋሉ፡፡
የቤታቸው ጣራ የተበሳሳ በመሆኑ ዝናብ ሲዘንብ ሳፋ (መዘፍዘፊያ) በመደቀን ችግሩን ማቃለል ቢችሉም ቤታቸውን አቋርጦ የሚያልፈውን ጎርፍ ግን የሚገቱበት አቅም አልነበራቸውም፡፡ የመጣውን መከራ በፀጋ መቀበል ብቸኛው እጣ ፈንታቸው ነበር፡፡ ይህም የሙት ልጆችን ለማሳደግ ምን ያህል ፈተና ደቅኖባቸው እንደነበር በትካዜ ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስታውሳሉ፡፡
ይህን ችግራቸውን የተረዱ የአካባቢው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ነዋሪዎችና ባለሃብቶች ተሰባስበው ቤታቸውን አፍርሰው እንደገና በብሎኬት ሰርተውላቸዋል፡፡ አሁን የመኖሪያ ቤት ችግራቸው ተቀርፎላቸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቅርቡ አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር የበጎ ፍቃድ ተግባራት እና የኮሪደር ልማት ስኬት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ከተሞችም መነቃቃትን የሚፈጥር የህዝብ እና የመንግሥት የትብብር ውጤት ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ያለ ከተማ ፕላን የተገነቡ፣ ያረጁና ያፈጁ ሰፈሮችን ለአኗኗር ምቹ በሆነ ደረጃ እንደገና ማደስ፣ ለሰውና ለትራንስፖርት የማይመቹ መንገዶችን ደረጃቸውን ጠብቀው መገንባት፣ እንዲሁም ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ያለ ልዩነት የሚጠቀሙበትን የህዝብ መዝናኛዎችን በማስፋፋት ረገድ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ከንቲባ አዳነች ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይንና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር)፣ ከተሞች ከሰው ልጅ ጋር ይመሰላሉ ይላሉ፡፡ “ሰው ይወለዳል፣ ይታመማል፣ ይታከማል፣ ይድናል ትውልድ ይቀጥላል፡፡ ከተሞችም በአንድ ወቅት ይመሰረታሉ፣ ያረጃሉ፡፡ መልሶ ማልማት ለትውልድ ዘላቂ ከተማ ከማስረከብ አኳያ መደረግ ያለበት ነው” ብለዋል፡፡
እንደ ዳንኤል (ዶ/ር) ገለጻ፣ በዓለም ላይ በኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን በተለይም በ1850ዎቹ አካባቢ በርካታ ከተሞች መልሰው ታድሰዋል፡፡ የከተሞችን ችግሮች ምላሽ ለመስጠት ከተደረጉ ጥረቶች አንዱ ያረጁ ቤቶችን መልሶ ማደስ ነው፡፡ በተለይ የፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ እንደገና የለማችው አሁን አዲስ አበባ እየለማችበት ባለው ስልት ነው፡፡ ከተሞችን መልሶ ማደስ የሚለው ሃሳብ በዓለም ላይ የቆየ ተግባር ነው፡፡ አሁኑ አዲስ አበባም ከዳግም ማልማት ጋር ተያይዞ ሰፊ ልምድና ተሞክሮ አዳብራለች፡፡
የከተማ መሰረተ ልማት ለሰው የሚያስፈልጉ የእለት ከዕለት የሚጠቀሙበት ጉዳዮች እና በስታንደርድ መመራት አለባት የሚሉት የከተማ ፕላን ባለሙያው፣ በዚህም ከተማዋ ውብ እና ጽዱ መሆን አለባት ብለዋል። ለከተማዋ እድገት ያረጁ ቤቶችን በበጎ ፍቃድ መርሃ ግብር እና ሌሎች አማራጮች መልሶ ማልማት ትልቅ ጉዳይ እና የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ደረጀ ካሳ እንደገለጹት፣ በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመዲናዋ በርካታ በጎ ፈቃደኞች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ላይ እየተሳተፉ ነው ብለዋል። የአቅመ ደካማና አረጋውያን ቤት እድሳት፣ የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት፣ ደም ልገሳና የትራፊክ አደጋን መከላከል ከሚሰጡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በበጎ ፈቃደኞች ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ማዕድ በማጋራትና ለአቅመ ደካሞች ቤት እድሳትና ግንባታ ዘርፍ ስኬታማ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል። ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 6 ሺህ 500 ቤቶችን ለማደስ ታቅዶ ወደ 6 ሺህ 730 ቤቶችን በማደስ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም 3 ሺ 500 ቤቶችን ለመገንባት እቅድ ተይዞ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ 2 ሺህ 100 ቤቶችን መገንባታቸውን አስታውቀዋል። በአዲስ አበባ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ብቻ እስከ አሁን ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት መቻሉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በይግለጡ ጓዴ