ብልፅግና ፓርቲ የበለጸገችና ጠንካራ ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን እየገነባ ነው-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

You are currently viewing ብልፅግና ፓርቲ የበለጸገችና ጠንካራ ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን እየገነባ ነው-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

AMN – የካቲት 15/2017 ዓ.ም

ብልፅግና ፓርቲ የበለጸገችና ጠንካራ ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን እየገነባ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

ፓርቲው ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ ወደ ከፍታ የሚወስዱ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት በሸገር ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ህዝባዊ ኮንፈረንስ ላይ ነው።

ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ፣ በዲፕሎማሲ እና በሌሎችም ዘርፎች ስኬቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ ወደ ከፍታ የሚወስዱና የህዝቡን መሻት የሚያረጋግጡ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ነው ያብራሩት።

እንደ አቶ አረጋ ገለጻ፥ ፓርቲው በ2ኛ መደበኛ ጉባኤው የኢትዮጵያንና የህዝቧን ጥቅም የሚያስጠብቁ እንዲሁም ሀገሪቱ በዓለም ተገቢውን ስፍራ እንድትይዝ የሚያደርጉ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

በመሆኑም የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በመተግበር ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካትና የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በርብርብ ማፋጠን ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በመድረኩ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ፓርቲው ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ገዥ ትርክት እንዲፈጠር እየሰራ ነው ብለዋል።

ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልን በማዳበር ዘላቂ የሰላም ግንባታን ለማፋጠን አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸው፥ ለስኬቱ የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ብልፅግና ፓርቲ ለሰላማዊ ውይይት ሁልጊዜም በሩ ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል።

የፓርቲው ምክር ቤት አባልና የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መሠረት አሰፋ ብልፅግና ፓርቲ የኢኮኖሚ ስብራቶችን በመጠገን በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ጠቅሰው፥ በተለይ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና እንድታደርግ ማስቻሉን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በመደመር እሳቤ የተመዘገቡ ድሎችን በማስቀጠል የሀገር ግንባታ ግባችንን እናሳካለንም ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review