AMN – ጥር- 18/2017 ዓ.ም
ብልፅግና ፓርቲ በመጀመሪያ ጉባኤው በገባው ቃል መሰረት የሴቶች ህፃናትና ወጣቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሯ ፓርቲው በመጀመሪያው ጉባኤ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች የፈጸማቸውን ተግባራት በተመለከተ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት ራዕያችን በ2022 የዜጎች መብትና ጥቅም የተከበረባት፤ ማህበራዊ ጥበቃ የተስፋፋበት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው።
ከዚህ በመነሳትም ብልፅግና ፓርቲ የሴቶችንና ወጣቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሴቶች በህግ አውጪ፣ በህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚ አካላት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከለውጡ በፊት ከነበረበት 23 በመቶ ወደ 35 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ዜጎች በመረጡት አደረጃጀት የመደራጀት መብትና ጥቅማቸውን ማስከበር እንዲችሉ ባከናወናቸው ተግባራት የመደራጀት ምጣኔ ከ10 ወደ 40 በመቶ አድጓል ብለዋል፡፡
በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል ረገድም ዓለም አቀፍ እውቅና የተገኘበት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው በገጠር ምንም አይነት ጎጂ ድርጊቶች የማይፈምባቸው ቀበሌዎች ቁጥር ከ1ሺህ በላይ መድረሱን ጠቁመዋል።
ከለውጡ በኋላ በተለይም በገጠር የሴቶች የመሬት ባለቤትነት ከ38 ወደ 62 በመቶ ማደጉን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ የቁጠባ አቅማቸውን ከ16 በመቶ ወደ 49 በመቶ ማሻሻልና የቆጠቡትን በአግባቡ መጠቀም መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በማስፋፋት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ከመቀነስም ባለፈ ጥቃት ሲደርስ ተጎጂዎቹ በፍጥነት አገግመው ወደ ማህበረሰቡ የሚቀላቀሉበት የማገገሚያና የማሰልጠኛ ማዕከላትን ማስፋፋቱን አንሰተዋል፡፡
ህፃናት የቀጣይ የኢትዮጵያ የብልፅግና መሰረቶች መሆናቸውን በመገንዘብም በቀዳማይ ልጅነት መርሀ ግብር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በዚህም እስከ ቀበሌ ባለው አደረጃጀት የህፃናት ፓርላማ በማደረጃት ህፃናት ድምፃቸው የሚሰማበት ሥርዓት መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡
ጎዳና ላይ የነበሩ ህፃናትን በማንሳት ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ቤተሰብ የሌላቸው ወደ ማቋቋሚያ ማዕከል እንዲገቡ መደረጉንም ተናግረዋል።
ወጣቶች በህግ አስፈፃሚ አካላት ያላቸው ፖለቲካዊ ተሳትፎ 10 በመቶ ብቻ እንደነበር አስታውሰው፤ ይበልጥ እየጨመረ በሚሄድ መልኩ ወደ 18 በመቶ ከፍ ማለቱንም አንስተዋል።
ብልፅግና ፓርቲ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በማህበረሰብ የጥምረት አገልግሎት ከ600 ሺህ በላይ ዜጎች እርስ በእርስ የሚረዳዱበት ሥርዓት መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡
የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግም ሀገር አቀፍ የወጣቶች ካውንስል እንዲመሰረት መደረጉን ሚኒስትሯ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።