ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ በመግዣና በመሸጫ መካከል ያለው ልዩነት ከ2 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት አሳሰበ

You are currently viewing ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ በመግዣና በመሸጫ መካከል ያለው ልዩነት ከ2 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት አሳሰበ

AMN- ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ይፋ ባደረገው አዲስ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲ፤ የውጭ ምንዛሪ በመግዣና በመሸጫ መካከል ያለው ልዩነት ከ2 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት አሳስቧል፡፡

አዲሱ የምንዛሬ ተመን አሰራር ይፋ መሆኑን ተከትሎ በውጭ ምንዛሪ ገበያው ላይ ያሉ ሂደቶችን ሲከታተል መቆየቱን ብሔራዊ ባንክ ገልጿል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ መካከል ያለው ልዩነት ዓለም አቀፍ አሰራርን መሰረት ያደረገ መሆን እንዳለበት ለባንኮች በላከው ደብዳቤ ማሳወቁን ጠቁሟል።

ባንኮች የውጭ ምንዛሪ መግዣ ዋጋቸውን ከመሸጫቸው ማቀራረብ እንዳለባቸው ከዚህ ቀደም በርካታ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡበት እንደነበረ ብሔራዊ ባንክ አስታውሷል።

ይሁንና ባንኮች የምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ ዋጋቸውን በራሳቸው እና ከደንበኞቻቸው ጋር ባላቸው ስምምነት የገበያውን ሁኔታ ግልፅና የአሰራር ሥርዓትን መሠረት ባደረገ የማስተካከል ነፃነት እንዳላቸው ጠቁሟል።

ባንኮች ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዙ ክፍያዎችንና ኮሚሽኖችን ለደንበኞቻቸው በተናጠል ማሳወቅ እንደሚኖርባቸውም አስገንዝቧል፡፡

ባንኮች ተወዳዳሪ ክፍያዎችን ሲያቀርቡም ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቃኘት ሊሆን እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም ባንኮች የኮሚሽን ወይም ተያያዥነት ያላቸው ክፍያዎችንና ከደንበኞቻቸው ጋር የሚያደርጓቸው የገንዘብ ልውውጦችን በግልጽ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡

እነዚህ የክፍያ ሂደቶችም ለብሔራዊ ባንክ በተለመደው መልኩ በመደበኛነት ማሳወቅ እንደሚገባ አመላክቷል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ውሳኔዎችም ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆኑ ማዘዙን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review