AMN – ጥቅምት 14/ 2017 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሩሲያ ካዛን እየተካሄደ ባለው የ16ኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያ ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርጉ የባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ የምታደርገውን ተሳትፎ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
ዓለም የገጠማት ካለው ፈተና አንጻር ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ጥበብ የተሞላበት አካሄድ እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት።
በተለይም የታዳጊ ሀገራት ኢኮኖሚ ፍትኃዊ ባልሆነ የዓለም ፋይናንስ ሥርዓት እየተፈተነ ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ ይህም ሥራ አጥነትና የዋጋ ንረትን እያስከተለ ነው ብለዋል።
ከዚህ አኳያ ብሪክስ የተሻሉ እድሎችን ይዞ መምጣቱን ነው የተናገሩት።
የዓለምን ግማሽ ያህል የሚጠጋ የሕዝብ ቁጥር የሚይዘው ብሪክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍትኃዊ ሥርዓትን በማስፈን ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።
በብሪክስ ሀገራት መካከል ጠንካራና አብነት የሚሆን ግንኙነት መፈጠር እንዳለበትም አውስተዋል።
አባል ሀገራቱ በተለይ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መስክም ተቀራርበው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ያስተላለፉት።
ብሪክስ ፍትኃዊና አካታች የዓለም ሥርዓት ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንደሚያበረክም ተናግረዋል።
በተለይም ታደጊ አገራት በዓለም አቀፍ መድረኮች ድምጻቸው እንዲሰማ በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ ስለመሆኑም ነው ያነሱት።
አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ፍትኃዊ ውክልና እንዲኖራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የጉባኤው ተሳታፊ ሀገራት ተመሳሳይ አቋም እንደሚኖራቸውም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የአፍሪካ ጥያቄ የውክልና ብቻ ሳይሆን የፍትኃዊነት ጉዳይ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ከሳሃራ በታች 3ኛውን ግዙፍ ኢኮኖሚ የያዘችው ኢትዮጵያ ያላት ወጣት አምራች ኃይል፣ ለም መሬትና ታዳሽ ኃይል ምቹ የኢንቨስትመንት መዳራሻ እንደሚያደርጋትም መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገችው የምትገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አዳዲስ የዕድገት መንገዶችን መክፈቱንም እንዲሁ።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገችው ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የአየር ንብረት ልውጥን የማይበገር የኢኮኖሚ እድገት ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያመላክት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።