ብርሃናማዋ ከተማ

You are currently viewing ብርሃናማዋ ከተማ

በታሪክ መንገድ ላይ ደልቶን ለመራመድ፣ በሙሉ ልብም ወደፊት ለመስፈንጠር ወደ ኋላ መንደርደር ግድነውና ይህንን ለትውስታ እናንሳ፡፡ የአዲስ አበባ የውበትም ሆነ የስልጣኔ እምብርት እየተባለ የሚጠራው የፒያሳዋ አራዳ መሆኑን ብዙ ፀሐፍት መስክረዋል፡፡ አራዳ፣ በሀገራችን ብዙ የመጀመሪያ የሚባሉ ነገሮች የተጀመሩበት ስፍራ ነው፡፡ እንዲያውም በብዙዎች ዘንድ አራዳ፣ ማለት “ዘመናዊነትን የሚከተል” እንደሆነም ይነገራል፡፡ አዎ እነ! ሜሪ አርምዴ፣ እነ አስናቀች ወርቁ፣ እነ ፋንቱ ማንዶዬ…..ጥበብን ከዘመናዊነት ጋር ያቋደሱበት፣ እነ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ዘጠኟን አለም አስር ያደረጉበት…ድንቅ ስፍራ ነው አራዳ፡፡

በ40ዎቹ እና በ50ዎቹ ዘመናዊ ሙዚቃ፣ ፋሽን እና የምሽት ህይወት አዲስ አበባ ውስጥ በተለይ አራዳ አካባቢ አብቧል ትለናለች በመጋቢት 1965 ዓመተ ምህረት የታተመችው መነን መፅሔት፡፡ ደግሞም ከዚህ ጋር ተያይዞ ስማቸው በዋናነት ይጠቀሱ ከነበሩት መካከል ሜሪ አርምዴ አንዷ ነበረች። እነ ሜሪ አርምዴ፣ ዘመናዊ ዳንስን እና የሴቶችን ፀጉር ቤት…..የጀመሩበት….ያስተማሩበት …..ስፍራ ነው አራዳ፤ ፒያሳ፡፡ አሁንም አዲስ አበባን እንደ አዲስ የወለደው ልማትም ከፒያሳ ጀምሯል፡፡

ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር “ትኩሳት” ብሎ በጠራው መጽሐፉ ጀርባ ፒያሳ ሂድ፤ “ፒያሳ፣ ወደ ሕይወት ትመልስሃለች” እንዳለው፡፡ መሐመድ ሰልማን ደግሞ “ፒያሳ ማህሙድ ጋ ጠብቂኝ” በተሰኘ ድንቅ ድርሰቱ የፒያሳን ውበት እንደ ጅረት እያፈሰሰ፣ እንደ ወንዝ እያገማሸረ አስኮምኩሞናል፡፡ “ፒያሳ አንድ ሺህ አንድ መቶ ካፌዎች ያሉባት ቅመም የሆነች ሰፈር ናት፡፡ አንድ ሺህ አንድ መቶ ቆንጆ ልጃገረዶች ደግሞ በካፌዎቿ ውስጥ ተኮልኩለው ኮካ በ‘ስትሮ’ ይጠጣሉ፡፡ ‘ስትሮ’ ምን እንደሆነ ካላወቅክ የፒያሳ ልጅ አይደለህም ማለት ነው። ‘ስትሮ’ በቆንጆ ልጅ ከንፈርና በቆንጆ ብርጭቆ መሀል የተሰራ የላስቲክ ድልድይ ነው” እያለ ፒያሳን አንቆለጳብሷታል፡፡ በርግጥ ይህ በዘመኑ እውነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ አበባ የትናንት ውበቷ በዘመን ጉም ተሸፍኖ ከዘመኑ እየራቀ በመንጎዱ ብዙዎቹን ማስቆጨቱ “ስሟ አዲስ፤ እሷ አሮጌ” የመባሉ ነገር የአዘቦት ተረክ ሆኖ መቅረቱም የማይካድ ሀቅ ነበር፡፡

የእውነት ዶሴዋ ሲገለጥ፣ አዲስ አበባ ዕድሜ፣ ወዝ፣ ለዛና ታሪክ ጠገብ ከተማ ናት።  የሀገሪቱም ሆነ የአህጉረ አፍሪካ የስልጣኔ፣ የነፃነት፣ የአንድነት፣ የጀግንነት በር፣ የተስፋም መስኮት ናት፡፡ ግና ዕድሜዋ እየገፋ፣ አዳሿ እየጠፋ፣ እርጅና ተጫጭኗት የስሟ ነገር አዲስ አበባ፣ “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” እንዲሉ የንፅህና ጉድለቷ ውበቷን አደብዝዞት፣ አብረዋት ያረጁ መንገዶችና መንደሮቿ፣ በድሮ ዝናቸው ብቻ ቀርተው፣ እንኳን ውበት ሊጨምሩላት ይቅርና አልፎ አልፎ እንደ ፈርጥ ጣል ጣል ያሉትን ጥቂት ድምቀቶቿን አደብዝዘውባት እንደነበር ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ የአዲስ አበባ ፀሐይ ደመናውን ገፍፋ፣ የታሪካችን እምብርት በሆነው በዓድዋ ድል መታሰቢያ በኩል አድርጋ፣ ዳግም በፒያሳ ላይ ወጥታለች። ፒያሳም እንደ አዲስ ተወልዳለች፡፡ አዲስ ውበትን ተጎናፅፋ፣ ቀንም ሌሊትም ደምቃ ትታያለች፡፡

በኮሪደር ልማቱ ተጨማሪ ውበት የተጎናፀፈው ፒያሳ – አድዋ ድል መታሰቢያ አካባቢ

 አሁን መገን ያራዳ ልጅ አይፈራም ኪሳራ፣    

ጃኬቱን አስይዞ ገባ ሰንጋተራ የሚለው ዘፈን ተረት ሆኗል፡፡ አሁን የአራዳ ልጅ ጃኬቱን ሳያሲዝ፣ ሳይከስር፣ ሳይሰክር፣ ይልቅም ጥሩ ረፍትን አትርፎ ከዓድዋ ድል መታሰቢያ እስከ ሰንጋተራ በዘለቀው ድንቅ የኮሪደር ልማት ዘና ብሎ ቀልቡ ወደ ፈለገው መጓዝ ይችላል። ምክንያቱም አዲስ አበባ ቀንም ሌትም ፈክታ የምትታይ ደግሞም የማታንቀላፋ ፍልቅልቅና ሰላማዊ ከተማ ናትና፡፡

ትናንት የውቤ በረሃዋ አስናቀች ወርቁ፣ ክራሯን በፍቅር እየገረፈች በአፍሪካ አንድነት ምሥረታ ወቅት “አማረች አዲስ አማረች” እያለች አገር ምድሩን እንዳስደመመችው  ዛሬ ደግሞ ቀና ብላ አዲስ አበባን ብታያት፡-

በውበት ላይ ውበት ቁንጅናን ደርባ፣

የትላንቷ ንግስት የእኔ አዲስ አበባ፣

ቀንም እንደ ፀሐይ ሌት እንደ ጨረቃ፣

በዘመን ዘምና ትታያለች ደምቃ፡፡የምትል ይመስለኛል፡፡

በቅርቡ በከተማዋ የተጀመረው፣ ዋና ዋና መንገዶችን የማስዋብ፣ የእግረኛ መንገድን የማስፋት፣ መዝናኛ ቦታዎችን የመገንባት እንዲሁም የመንገድ ዳር መብራት እና ቴሌኮሚዩኒኬሽን መስመሮችን በዘመናዊ መንገድ የመዘርጋት ሥራው (የኮሪደር ልማት) ለመዲናዋ ትንሳኤ አሊያም እንደ አዲስ መወለድ ምክንያት እንደሆነ ብዙዎች በመመስከር ላይ ናቸው፡፡

በዚህ መርሃ ግብር የከተማዋን ታዋቂ እና ነባር አካባቢዎችን የሸፈነው የመጀመሪያው ምዕራፍ አምስት መስመሮችን የያዘ ነው። በዚህ ምዕራፍ ግንባታ ከተከናወነባቸው አካባቢዎች መካከል ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ቦሌ፣ መገናኛ፣ ሜክሲኮ እና ሲ.ኤም.ሲ ይገኙበታል። እነዚህ ስራዎች ከተማዋን ከማያንቀላፉ ከተሞች መካከል አንዷ እንዳደረጓት ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን እየዘገቡት ነው፡፡

እኛም ከፒያሳ የጀመርነውን ቅኝት አራት ኪሎ፣ ቦሌ፣ መገናኛ፣ ሜክሲኮ እና ሲ.ኤም.ሲ በገሃድ የተመለከትነውን፣ በምናብ አክናፍ እየበረርን፣ በብዕር አፍ እየተነጋገርን፣ እፍታ እፍታውን አብረን እንኮመኩማለን፡፡

ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ በሚወስደው መንገድ ላይ ነን፡፡ በግራና በቀኝ የነበሩ ታሪካዊ ቤቶች ታድሰው ትናንትን ከዛሬ ጋር ለማስታረቅ የቆሙ እና ግርማ ሞገስን የተጎናፀፉ ሽማግሌዎችን ይመስላሉ፡፡ ቅርስን ጠብቆ ከተማን እንዴት ማስዋብ እንደሚቻልም አስተማሪ ናቸው፡፡ ከሲኒማ አምፒር ቀጥሎ ያሉ ጥቂት እና ውብ ታሪካዊ ህንፃዎችን አለፍ እንዳልን ለዐይን የሚያሳሱ እና ነፍስያን በሀሴት ዝናብ የሚያረሰርሱ እፅዋትን እንመለከታለን። እንደ ኮበሌ ፀጉር ጥቅጥቅ ብለው በበቀሉት ሳሮች መካከል አልፎ አልፎ የተተከሉት እና እንደ ስልጡን ሰራዊት ሰልፋቸውን ይዘው የቆሙት ዘንባባዎች ደግሞ የክብር ዶክተር ጥላሁን ገሰሰን፣ “የዘንባባ ማር ነሽ ወለላሽ የረጋ፣ አልደርስብሽ  አልኩኝ እጄን ብዘረጋ” የሚለውን ድንቅ ዜማ ያስታውሰናል፡፡

“አንጎላችን ልክ እንደ ሆዳችን ባዶ ሲሆን፣ የማስጠንቀቂያ መልዕክት አይሰጠንም” የሚለው የአረቦች አባባል ሚዛን የሚደፋው አሁን ነው። በርግጥም ግፊያና ግርግር በበዛበት ከተማ ተፈጥሮ ነፃነቷን አግኝታ ውበቷን እና ጉልበቷን በእፅዋት መካከል ስትገልጥ ላየ ሰው አዕምሮው ምን ያህል ተርቦ እንደነበር መረዳት ይቻለዋል፡፡

እ.አ.አ በ1945 ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የራስ መኮንን ድልድይ በሚገርም ፍጥነትና ጥበብ እንደ አዲስ እየተሰራ መሆኑን ሲመለከቱ ደግሞ ባለው ላይ መጨመር ምን ያህል ልብን እንደሚሞላ ያረጋግጡበታል። ድልድዩን እንደተሻገሩ የትናንቱ ሰባ ደረጃ ታሪክና ወዙን ጠብቆ በውበት ላይ ውበትን ተጎናፅፎ ጥቂቶች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ዘና እንዲልበት ደረቱን አስፍቶ፣ ፊቱን አፍክቶ፣ በምሽቱ መሐል ለብቻው ፀሐይ የወጣችለት ይመስላል፡፡ በርግጥም የዘመን ፀሐይ በአንዳንድ ስፍራዎች እንደወጣች ለማረጋገጥ ዘወር ዘወር ብሎ መመልከት በቂ ነው፡፡

አራዳ ክፍለ ከተማና ዙሪያውን የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ ከተማን ከተፈጥሮ የማስማማት  ስራዎችን አድንቀን ወደ ድል ሀውልት ስናመራ የውስጥ ለውስጥ የእግረኛ መንገዱን፣ ከላይ ደግሞ የሀውልቱ ዙሪያ ጌጦችን፣ በዙሪያው ያሉ እና እንደ አዲስ ነፍስ ዘርተው የቆሙ ሕንፃዎችን በቀን ብቻ ሳይሆን በማታ ለተመለከታቸው የማያንቀላፉ ከተሞች ምንኛ ውብ መሆናቸውን በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡

ከአራት ኪሎ መገናኛ በሚወስደው መንገድ በተለምዶ ‘ቤሊየር’ ተብሎ ወደሚጠራው ስፍራ ስናቀና ለካ! የከተሞች ልብስ፣ ግርማና ሞገስ፣ የህንፃ ጫካ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ እፅዋትም መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ የህንፃዎች ውበት የሚፈካው በቁመታቸው ርዝመት፣ በደረታቸው ስፋት ሳይሆን በዙሪያቸው ባሉ አረንጓዴ ተክሎች እንደሆነም እንዲሁ፡፡

በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ከደመቀ እሱነቱ ጋር እንደ ንጋት ኮከብ ፈክቶ የሚታየውን ‘የኮከበ ፅባህ’ ትምህርት ቤትን አድንቀን፣ ወደ መገናኛ ስናመራ በግራም በቀኝም ያሉ ውብ ስፍራዎች በተፈጥሮ ዛፎች እና በዘመናዊ የመንገድ ዳር መብራቶች ድንቅ ብርሃን ፈክተው ሌቱን ቀን አስመስለውታል፡፡ መገናኛ በትክክልም ከስሙ ጋር የተወዳጀ ይመስላል፡፡ በርካታ የትራፊክ እንቅስቃሴዎችን ገድቦ የነበረው አደባባይ ተነስቶ እንደልብ ፈልሰስ ለማለት ያስችላል። በማታንቀላፋው ከተማም ልክ እንደቀኑ ሁሉ ወደ ቦሌም ወደ ጉለሌም የሚሄደው ብዙ ነው። የተለያዩ የንግድ ተቋማትም በብዙዎቹ አካባቢ በሚባል ደረጃ እንደቀኑ ደምቀው ይታያሉ፡፡

አብዛኛዎቹ ሕንፃዎች ተመሳሳይ ቀለም እየተቀቡ በመሆኑ ልክ ከአንድ ማህፀን እንደወጡ መንትዮች አንዱን ከአንዱ ለማበላለጥ ያስቸግራል፡፡ ስርዓት በሌለውና በተለያዩ ቀለማት ማረፊያ አጥተው የነበሩ ዐይኖች እፎይ ያሉም ይመስላል፡፡ በተለይም ከመገናኛ ሲ.ኤም.ሲ የሚወስደው መንገድ በመኪና ብቻ ሳይሆን በእግርም ማለፊያ! ነው፡፡ ቆም ብሎ ላማተረውማ የመንፈስ ምግብ ነው፡፡ እስከ ሲ.ኤም.ሲ አደባባይ በቀን ይቅርና በምሽት የተጓዘ ሰው ከተማዋ ምን ያህል እንደተለወጠች እራሱ ምስክር ይሆናል፡፡

በመስቀል አደባባይ ሲያሻን ወደ ቦሌ፣ ሲለን ወደ ሜክሲኮ፣ በምሽት ብንጓዝ አዲስ አበባ በርግጥም ብርሃናማ ከተማ እየሆነች መምጣቷን ሃያ አራት ሰዓት ለስራም ለመዝናኛም ምቹ መሆኗን እና የማታንቀላፋ ከተማ ሆና እንደ አዲስ እየተሰራች ስለመሆኗ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

ኮሪደር ልማቱ በቦሌ ከፊል ገፅታ

አዲስ አበባን የማታንቀላፋ ከተማ ያደረጓት የኮሪደር ልማት ስራዎች በራሳቸው ያለ ማንቀላፋት የተሰሩ ናቸው፡፡ ቀንና ሌሊት ሳምንቱን ሙሉ ለልማት በተዘረጉ በርካታ እጆች የታነፁ፣ አዲስ የስራ ባህልን ያስተዋወቁም ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጅኒየር ደቦ ቱንካ፣ በመዲናዋ የተገነቡ አዳዲስ ፕሮጀክቶች አዲስ የስራ ባህልን ያስተዋወቁና በግንባታው ዘርፍ ወደ ኋላ የቀረንበትን ጊዜ የሚያካክሱ መሆናቸውን መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

በሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የተገኘው ውጤትና አዲስ የስራ ባህል በከፍተኛ ጥረት የተገኘ ነው፡፡ በሌላ በኩል የሌሊት ስራ ብርሃን የማቅረብ ጉዳይ እንጂ ከቀኑ ብዙም የተለየ አይደለም። አለፍ ሲልም በሌሊት ስራ ሰው አቅም ካገኘ ውጤታማ ይሆናል፡፡ አየሩ ቀዝቀዝ በሚልበት ጊዜ መስራት በራሱ ለሰው ብቻ ሳይሆን ለማሽኖች ጤና የበለጠ ይደግፋል።

ይህን መሰል የስራ ባህል ለሀገር የሚያመጣው ትሩፋት በጣም ከፍ ያለ ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱ የደከመ የስራ ባህላችንን የሚቀይር ነው። በሌላ በኩልም በጊዜ ርዝመት ምክንያት የሚፈጠሩ የፕሮጀክትና የአገልግሎት መጓተቶችን ያስቀራል። እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ከተማ ብዙ ያልተሰሩ የቤት ስራዎች አሉን፡፡ ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በጊዜ የለኝም እሳቤ መስራት እዳዎችን የሚያራግፍ ስትራቴጂ በመሆኑ ህዝባችንን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ይህን መሰል የስራ ባህል መዳበር ወደ ኋላ የቀረንበትን ጊዜ ማካካሻ ነው፡፡ ይህም የሀገሪቱን ዕድገት ያፋጥናል ማለታቸውን አዲስ ልሳን ጋዜጣ ዘግባ ነበር፡፡ በርግጥም አዲስ አበባ ተፈጥሮ የለገሰቻትን ጊዜ በአግባቡ እየተጠቀመችበት ይመስላል፡፡ በቀን ብቻ ሳይሆን በሌሊትም እየሰራች፣ እያበራች! መሆኑን በርካቶች በመመስከር ላይ ናቸው፡፡

የስነ ልቦና ምሁራን የማይተኙ ከተሞችን “የዓለም የልብ ምት ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሃያ አራት ሰዓት ስለማያንቀላፉ፣ ዓለማችን ሕይወት ዘርታ እንድትኖር ያደርጋሉና” ሲሉ ይገልጿቸዋል። ዋና መቀመጫውን ቶኪዮ ያደረገው “ዘ ጃፓን ታይምስ” የተሰኘው የሚዲያ ተቋም የማያንቀላፉ ከተሞች ሲል በሰራው ጥናታዊ ዘገባ፤ ቶኪዮ፣ ኒው ዮርክ፣ ባንኮክ፣ ዱባይ እና አዲስ አበባን የመሳሰሉ ከተሞች ሃያ አራት ሰዓት ንቁ በመሆናቸው “እንቅልፍ ለምኔ” ብለዋል ይለናል፡፡

በርግጥም አዲስ አበባ በባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዋ የተነሳ  የ24/7 አገልግሎት መስጠት ግድ ይላታል፡፡ ለአፍሪካ ዲፕሎማሲ እና ንግድ ቁልፍ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን እስከ ምሽት ድረስ ንቁ በመሆን ብዙ ታተርፋለች፣ ለብዙዎችም ትተርፋለች። ትናንትን ከዛሬ፣ ባህላዊውን ከዘመናዊው፣ አዋህዳ የያዘችው ይህች የብዝሃነት አንባ! እንደ ስሟ አዲስ እየሆነች ነው፡፡

በኋላ ጣፋጭ ነገር ሆኖ እንዳይቆጨን “አልበላም ብሎ መማል፣ ወጥን ቀምሶ ነው” እንዲል የሀገሬ ሰው፣ ስለ ምግብ ካነሳን አይቀር በተለይ የኮሪደር ልማቱ በሚያካልላቸው ስፍራዎች ልዩ ልዩ ምግብና መጠጦችን የሚያቀርቡ ዘመናዊ ሱቆችም አሉ፡፡ ደግሞም ከተበላ ከተጠጣ ሆድ ስራውን አያቆምም እና “ጽዱ ጎዳና-ኑሮ በጤና”  በሚል ንቅናቄ በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ የተገነቡ ምቹ የወገብ መፈተሻ ስፍራዎች ስላሉ እንቅስቃሴዎት የተቃና ይሆናል፡፡ ስለሆነም መተቸትም ሆነ ማመስገን አይቶ ነውና በቀንም በማታ ዘወር ዘወር እያላችሁ እንደ አዲስ የተወለደችውን ከተማ ተመልከቱ፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review