የመማሪያ ክፍሎቹ ጽድት ያሉ፣ ልዩና ዘመናዊ ናቸው፡፡ በአንድ ክፍል ውስጥ 16 ተማሪዎች ብቻ ተቀምጠው የሚማሩ ሲሆን፤ የወንበር እና ጠረጴዛዎቹ አቀማመጥ ለክፍሉ የተለየ ውበት ከመስጠታቸው በተጨማሪ ለመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ተማሪ ጠረጴዛ ላይ በብሬል ወረቀት ላይ የአይነ ሥውራን መፃፊያ slate stylus እና የብሬል ወረቀት ተቀምጦበታል። በክፍሉ ውስጥ ለሁሉም አማካይ በሆነ ቦታ ላይ በብሬል የተጻፈ መጽሐፍ ተቀምጧል፡፡ ይህ የመማሪያ ክፍል የሚገኘው በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አስተባባሪነት ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው ብርሀን የአይነስውራን አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡
ትምህርት ቤቱ፤ በ41 ሺህ 300 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ይዞታ ላይ አርፏል። እኛም በዚህ ትምህርት ቤት የተገኘነው ለ2017 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማሩን ዋና ተግባር ለማከናወን ያደረገውን የዝግጅት ምዕራፍ ለመቃኘት ነው፡፡ በቅኝታችን ለማየት እንደቻልነው ትምህርት ቤቱ እጅግ ዘመናዊ እና ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ነው። የትምህርት ቤቱ ቅጥረ ግቢ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ሕንፃዎች እና መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል፡- የተማሪዎች ማደሪያ፣ መመገቢያ አዳራሾች፣ መጸዳጃ ቤቶች፣ አስፈላጊ ግብዓት የተሟላላቸው ቤተ ሙከራዎች፣ ጂምናዚየም፣ ክሊኒክ፣ የልብስ ማጠቢያ (ላውንደሪ)፣ የሰራተኞች ማደሪያ ይገኙበታል፡፡
ስለትምህርት ቤቱ የ2017 የትምህርት ዘመን ዝግጅት የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል የተለያዩ አካላት ሃሳባቸውን እንዲያጋሩ አነጋግሯቸዋል፡፡ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ክንድዬ በለጠ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው፡፡ ተማሪውን ያገኘነው ከጓደኛው ጋር በመሆን የመማሪያ ክፍሎችን ሲጎበኝ ነው፡፡ ክንድዬ ከ1 እስከ 7ኛ ክፍል የተማረው በደቡብ ጎንደር ነው፡፡ ከ8ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ በባህርዳር ከተማ ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ ለአይነ ስውራን የተሻለ ትምህርት የሚሰጥበትን ትምህርት ቤት ለመፈለግ ሲባል በአብዛኛው ከቤተሰብ የመራቅና ራስን በራስ የማስተዳደር ኃላፊነትን በመውሰድ የሚችለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ያልተገደበ ጥረት በማድረጉ አሁን ባለበት ምቹና ዘመናዊ ትምህርት ቤት ትምህርቱን የመከታተል ዕድል አግኝቷል፡፡ ይህም የወደፊት ህልሙን የሚያሳካበትን መንገድ ለመጀመር አቅም እንደሚፈጥርለት ተናግሯል፡፡
እንደ ተማሪ ክንድዬ ገለፃ፤ በዚህ ትምህርት ቤት ለመማር ዕድል ማግኘት እሱን ለመሰሉ ዓይነ ስውራን ኢትዮጵያዊ ተማሪዎች ዳግም እንደመወለድ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ በትምህርት ግብአት እና መሰረተ ልማት የተሟላ ነው፡፡ ለ2017 የትምህርት ዘመን የተደረገው ዝግጅት ከባለፈው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለም፡፡ የዘንድሮው በእጅጉ የተሻለ ነው፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት ለምንገኝ ተማሪዎች ያገኘነው ዕድል ለሁሉም እንዲሆን የሚያስመኝ ነው፡፡ ዋናውን ትኩረት ትምህርት ላይ ብቻ በማድረግ እየበሉ እየጠጡ፣ ምቹ አልጋ ላይ እየተኙ፣ በንጹህ አካባቢ እየኖሩና በብሬል እየጻፉ በተለየ መልኩ መማር መቻል አዲስ ህይወት የመኖር ያክል የሚቆጠር ነው፡፡
ተማሪ ተስፋዬ ለማ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው። ከ1 እስከ 4ኛ ክፍል ትምህርቱን የተከታተለው በተወለደበት አካባቢ በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሲሆን፤ የተማረውም ማየት ከሚችሉ ተማሪዎች ጋር ተቀላቅሎ ነው፡፡ ከ5 እስከ 8ኛ ክፍል ደግሞ በሰበታ የአይነስውራን ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከ9 እስከ 11ኛ ክፍል ያለውን ደግሞ በቡርቃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ 12ኛ ክፍልን ደግሞ በዚህ በብርሀን የአይነ ስውራን አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማር እድል አግኝቶ ተቀላቅሏል፡፡ ቀደም ሲል ያለፈባቸውን የትምህርት ተቋማት እና አሁን የተቀላቀለበትን የብርሃን ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ሁኔታ በማነፃፀር እንዲህ ሲል ይናገራል፤ “ቀደም ሲል የተማርኩባቸው ትምህርት ቤቶች በአብዛኛው ለዓይነ ስውራን ምቹ አልነበሩም። የግብዓት እጥረት ያለባቸው፣ የልዩ ፍላጎት መምህራን በበቂ ሁኔታ ያልተሟሉባቸው በመሆናቸው ለመማር ፈታኝ ነበር፡፡ ችግሩን ለማቃለል ሲባል የአዓነ ስውራን ትምህርት ቤቶች ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች ለመማር ከቤተሰብ ርቆ መሄድ ግድ ይላል፡፡ በዚህ ወቅት ከአዲስ አካባቢና ማህበረሰብ ጋር ከመተዋወቅ ባለፈ ለቤት ኪራይና ለሌሎች ወጪዎች አቅምን የሚፈታተን ሁኔታ መጋፈጥን ግድ ይላል፡፡ አሁንም ቢሆን በማህበሰቡ ዘንድ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚሰጠው አመለካከት ጫና ማሳደሩ አልቀረም። አሁን የመጣሁበት ትምህርት ቤት ከቀደሙት ጋር ሊነጻጸር የማይችል ነው፡፡ እውነት ለመናገር መጀመሪያ ስመጣ የቤት ኪራይ ለመሸሽ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በቦታው ደርሼ ያገኘሁት በትምህርት ዓለም ውስጥ እያለሁ አገኛለሁ ብዬ ያልጠበኩት ድንቅ ትምህርት ቤት ነው፡፡”
በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል እንደተወለደች እና አይነ ስውር በመሆኗ ከቤተሰብ ርቃ ለመማር እንደተገደደች የምትገልጸው ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ ሀና አስማረ ናት። በአሁኑ ወቅት ከዳግማዊ ሚኒሊክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደመጣች የምትናገረው ተማሪ ሀና አዲስ አበባ ከመግባቷ በፊት በሻሸመኔ የአይነ ስውራን ትምህርት ቤት ተምራለች። ቤት ተከራይታ ራሷን ታስተዳድር ስለነበር አለቀ አላለቀ እያለች ታስብ እንደነበርና አሁን ግን ራሷን ከመሰል ሃሳብ ነጻ አድርጋ እንድትማር የሚያደርግ በመሆኑ የእድለኝነት ስሜት እንደተሰማት ትገልጻለች፡፡ አለቀ ጎደለ ብሎ ከማሰብም በላይ መራብ መጠማት እንደነበር የምታስታውሰው ተማሪ ሀና አሁን ግን በቆየችበት ውስን ቀናት ግቢው በሁሉም ነገር ምልኡ እንደሆነና በእንዲህ አይነት ትምህርት ቤት እማራለሁ ብላ አስባ ስለማታውቅ በምናብ የምትኖር እንደመሰላትም የተሰማትን ስሜት ትገልጻለች። በከፊል የምታይ ከመሆኗ የተነሳም ከሌሎች አይነ ስውራን ተማሪዎች በተለየ የግቢውን ምቾች ማስተዋል ችላለች፡፡ ለአይነ ስውራን ምቹ ባልሆነና በቂ የግብአትና መሰረተ ልማት ባልተሟላበት ትምህርት ቤት ተምራ ውጤታማ መሆን መቻሏን በማስታወስ በእንዲህ አይነት የተሻለ ትምህርት ቤት ለመማር እድል ማግኘቷ ወደፊት ተምራ ከምታልመው ደረጃ ለመድረስ አቅም እንደሚሆናት ነው የገለጸችው፡፡
ሌላዋ በትምህርት ቤቱ ያገኘናት እና ሀሳቧን የሰጠችን ከወላይታ ሶዶ እንደመጣች የምትገልጸው የ11ኛ ክፍል ተማሪዋ ተስፋነሽ ታከለ ናት፡፡ ከ1 እስከ 4ኛ ክፍል ድረስ ወላይታ ሶዶ በአይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት በመማሯ ብዙም ችግር እንዳላጋጠማት ትገልጻለች፡፡ ከ5 እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ በወላይታ ሶዶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በክፍያ እዛው እያደረች ከአይናማዎች ጋር ተቀላቅላ ነው የተማረችው፡፡ 9ኛ እና 10ኛ ክፍል በወላይታ ሶዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማረች ሲሆን፤ ትኖር የነበረው ግን በግለሰብ ቤት ተከራይታ ነው። “ተከራይቶ መማር እንኳን አካል ጉዳት ላለበት ይቅርና ለሌላውም ቢሆን ኑሮ ፈታኝ እንደሆነ መገመት አያዳግትም” ስትል ሀሳቧን ትገልጻለች፡፡
ከአይናማዎች ጋር ተቀላቅላ መማሯ ብዙ ችግር ነበረው የምትለው ተማሪ ተስፋነሽ፣ በቃል ብቻ መስማት እንጂ ብሬል ባለመኖሩ ማስታወሻ መጻፍ አይቻልም ነበር፡፡ ምንም አይነት ግብአት ሳይኖር እኩል ፈተና ላይ መቅረብ ለውጤታማነት አሉታዊ ተጽእኖ ነበረው፡፡ ሆኖም በምታደርገው ብርቱ ጥረት የደረጃ ተማሪነቷን ሳትለቅ እዚህ ደረጃ ለመድረስ መቻሏን ገልጻለች፡፡
በዚህ ለአይነ ስውራን ተማሪዎች ተብሎ በተሰራው አዳሪ ትምህርት ቤት ከመጣች ሳምንት እንደሆናትና አስፈላጊ ግብአት የተሟላለት ከመሆኑ የተነሳ የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጋት፣ ተምራም ሀገሯን ለማስጠራት ምኞት እንዳላት ተማሪ ተስፋነሽ ተናግራለች፡፡
የብርሀን የአይነ ስውራን አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ርዕሰ መምህር አባይ ተስፋዬ ስለትምህርት ቤቱ የ2017 የትምህርት ዘመን ዝግጅት አስመልክተው ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተውናል። እንደሳቸው ገለፃ፤ ትምህርት ቤቱ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምር ሲሆን በዘንድሮው የትምህርት ዘመንም ወንድ 156፣ ሴት 156 በአጠቃላይ 312 አይነ ስውራን ተማሪዎችን ለማስተማር ተቀብሏል፡፡ ተማሪዎቹ ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ተመልምለው የመጡ ሲሆን የተመረጡበት መስፈርትም ውጤታማነታቸው ነው፡፡
ምክትል ርዕሰ መምህር አባይ እንዳስረዱት፣ ትምህርት ቤቱ ዝግጅቱን የጀመረው ከግንቦት ወር ጀምሮ ነው፡፡ ከትምህርት ቢሮ ጋር በመሆን ባለሙያዎችን የመመደብ፣ የትምህርት ቤቱ የመተዳደሪያ ደንብ፣ መመሪያ እና መዋቅር የማዘጋጀት እንዲሁም የ2017 ትምህርት ዘመን እቅድ ዝግጅት ተከናውኗል፡፡ ለተማሪዎቹ የመማር ማስተማር ዝግጅት እንደ መምህራን የመመልመል፣ የማደሪያና የመማሪያ ክፍሎችን በግብአት የማደራጀት፣ ለመማሪያ የሚያስፈልጉግብአቶች ለምሳሌ፡- የብሬል ወረቀት፣ የብሬል ወረቀት ላይ የአይነ ሥውራን መፃፊያ ስሌት ስታይለስ (slate stylus)፣ ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ በብሬል የተጻፉ ለመማር ማስተማር አጋዥ የሆኑ መጻህፍት በሚማሩበት ክፍሎች ውስጥ እንዲሟሉ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪ ሲንቀሳቀሱ የሚይዙት ነጭ በትር (ዋይት ኬን)፣ መነጽር፣ ክፍል ውስጥ በድምጽ ሲማሩ ድምጽ የሚቀዱበት ሪከርደር ለእያንዳንዱ ተማሪ የማሰራጨት ስራ ተሰርቷል፡፡ ለእያንዳንዱ ተማሪ የሚደርስ በኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ማህበር በኩል በብሬል የተጻፈ የመጻሕፍት ህትመትም በመባዛት ላይ ይገኛል፡፡
ትምህርት ቤቱ ከዚህም በተጨማሪ ዲጂታላይዝድ በሆነ ቤተ መጻህፍትም የተደራጀ ነው፡፡ በቤተ መጻህፍቱ በሚገኙ 30 ኮምፒዩተሮች ላይ “ጃውስ” የሚባል የማዳመጫ ሶፍትዌር ተገጥሞለታል። ሶፍትዌሩ አንደኛ የተጻፉ መጻህፍትን በድምጽ እንዲሰሙ ያደርጋል። እንዲሁም መረጃዎችን ከዩቱብ አውርደው እንዲያጠኑ ያግዛቸዋል፡፡ ሌላው የተለያዩ በብሬል የተጻፉ መጻህፍትን የሚያነቡበት ቤተ መጻህፍት ለተማሪዎቹ ተዘጋጅቷል፡፡ ከገጠራማው የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ፣ ምንም አይነት የብሬል እውቀትም ሆነ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትምህርት የሌላቸውና በመስማት ብቻ ተወዳዳሪ በመሆን የመማር እድል ያገኙ ተማሪዎችን ከመደበኛው የመማር ማስተማር ሂደት በተጓዳኝ ለማሰልጠን ትምህርት ቤቱ የመለየት ስራ ሰርቷል፡፡
የተማሪ መጻህፍት ጥምርታው አንድ ለአንድ ሲሆን፤ የተማሪ ክፍል ጥምርታ 1 ክፍል ለ16 እና የተማሪ መምህር ጥምርታም አንድ መምህር 16 ተማሪዎችን ነው የሚያስተምረው። ይህም የተማሪዎቹን ውጤታማነት ወደላቀ ደረጃ እንደሚያሳድገው የሚናገሩት ምክትል ርእሰ መምህሩ፣ ሌሎች አይነ ስውራን ተማሪዎች ጠንክረው በመስራት በዚህ እንደ አዲስ አበባ እንዲሁም እንደ ሀገር አልፎ ተርፎም እንደ አህጉር ብርቅዬ በሆነ ትምህርት ቤት ለመማር የሚያስችለውን እድል ሊጠቀሙበት ይገባል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ይህ በአይነቱ ልዩ የሆነ ዘመናዊ የአይነ ስውራን ትምህርት ቤት ግንባታ ተጠናቅቆ በተመረቀበት ወቅት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልእክት፤ በሀገር ደረጃ የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ትጋት 34 ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል። ከእነዚህ መካከል ይህ የአይነ ስውራን ልዩ ትምህርት ቤት አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ እስካሁን ድረስ አንድም ትምህርት ቤት በዚህ የጥራት ደረጃ አልተሰራም። ክሊኒክ፣ የሙዚቃ መማሪያ፣ ሁለት አይነት ቤተ መጻህፍት፣ ማደሪያና መመገቢያ እንዲሁም ለሰራተኞች ማደሪያ አለው በማለት የጥራት ደረጃውን ገልጸውታል፡፡ ለአይነስውራን ከንፈር መምጠጥ ብቻ በቂ እንዳልሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነሱን ታሳቢ ያደረጉ ምቹ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ ተገቢ በመሆኑም ይህ የአይነ ስውራን ትምህርት ቤት እንዲገነባ ተደርጓል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የብርሀን የአይነ ስውራን አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ2017 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ቅበላን በተመለከተ ባስተላለፉት መልእክት፤ “በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተሻለ ውጤት አምጥተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የገላን የወንዶች አዳሪ እና የመነን የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤቶች መቶ በ መቶ ማሳለፍ ችለዋል፡፡ ይህ የአይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ሲጨመር በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል የማፍራት ስራውን ውጤታማ ያደርገዋል” ብለዋል።
በለይላ መሀመድ