AMN – ጥቅምት 21/2017 ዓ.ም
ብቁ እና ተወዳዳሪ የሆኑ ተቋማትን መገንባት ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባል ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ ከቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ዲኖች እና ከዲፓርትመንት ተጠሪዎች ጋር የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀምን በተመለከተ ግምገማ አካሂዷል።
በዚህ የ2017 ሩብ ዓመት ግምገማ ላይ የቢሮው ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ተገኝተዋል።
በመድረኩ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተከናወኑ ተግባራት የቀረቡ ሲሆን በተለይ ዲጅታል የአሰራር ስርአት በመዘርጋት እና በማዘመን ረገድ በርካታ ስራዎች ስለመሰራታቸው ተመላክቷል።
ብቁ እና ተወዳዳሪ የሆኑ ተቋማትን መገንባት ቁልፍ ተግባር ነው ያሉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ቀልጣፍ የአሰራር ስርአትን ለመዘርጋት በአጫጭር ስልጠናዎች ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
በተቋሙ በተደረገው የሪፎርም ስራዎች ለተገልጋዩ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መቅረፍ መቻሉን ያነሱት አቶ ጥራቱ በአጫጭር ስልጠና የዳበረ ባለሙያን በመፍጠር ረገድ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ጥሩ ተሞክሮ ስለመኖሩና አሁንም ተጨማሪ ስራዎች እንደሚጠይቁ ጠቁመዋል።
ኮሌጆች ሰፊ ሀብትና ትልቅ የሰው ሀይል ያሉባቸው በመሆናቸው ብልሹ አሰራርን በማስቀረት ረገድ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ያሉት አቶ ጥራቱ ከስልጠናዎች ባሻገር የምዘና ስራዎች ላይም ቀጣይ የቤት ስራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።
በራሄል አበበ