AMN- ጥቅምት 20/2017 ዓ.ም
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያ ሁሉን አካታች እድገት እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ጉዞ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አስታወቀ።
ኢትዮጵያ የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እየተገበረች ያለውን የበጀት መርሃ ግብርም አድንቋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋሰው በተመድ የሴቶችን ጉዳይ የሚከታተለው ዩኤን ውመን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኒያራድዛይ ጉምቦንዝቫንዳ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ በስርዓተ ጾታ ፋይናንስ፣ የስርዓተ ጾታ እኩልነት ለማረጋገጥ እና ሴቶችን ለማብቃት እያደረገች የምትገኛቸው ጥረቶች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች የሴት መራሮችን ሚና ለማሳደግ፣ ሁሉን አቀፍ እድገት እውን ለማድረግ እና በሁሉም ደረጃዎች የሚሰጡ ውሳኔዎች አሳታፊ እንዲሆኑ አበክራ እየሰራች ነው ብለዋል።
ከዚህ አንጻር ዩኤን ውመን የኢትዮጵያ የስርዓተ ጾታ እኩልነት መከታተያ ስርዓት ለማሻሻል፣ የሴቶችን የፋይናንስ አቅም ለማጎልበት እና የሴቶች የፋይናንስ አካታችነት እና ተደራሽነት ለማረጋጋጥ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ድጋፎቹ በፋይናንስ አቅርቦት እና ተደራሽነት ያሉ ውስንነቶችን ለመፍታት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ስርዓተ ጾታን ያማከለ የበጀት ዝግጅት፣ የስርዓተ ጾታ የበጀት መግለጫ እና የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ያሳየችው መሻሻል በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።
ዩኤን ውመን በኢትዮጵያ ዘላቂ የስርዓተ ጾታ ፋይናንስ ስርዓት ለመዘርጋት እና ሴቶችን በማብቃት ዘላቂነት ያለው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለማምጣት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን መደገፉን እንዲቀጥል ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።
የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ በፌደራል እና በክልል ደረጃ የአቅም ግንባታ ስራ የማከናወን አስፈላጊነት አንስተዋል።
የዩኤን ውመን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኒያራድዛይ ጉምቦንዝቫንዳ ኢትዮጵያ የስርዓተ ጾታ እኩለነትን የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችን በመተግበር እየወሰደች ያለውን እርምጃ አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ የስርዓተ ጾታ እኩልነትን የሚያሻሽሉ ጠንካራ እና የሚደነቁ የበጀት ኢኒሼቲቮችን እየተገበረች እንደምትገኝ እና ይህም በቀጣናው ላሉ ሌሎች አገራት ምሳሌ መሆን የሚችል ነው ብለዋል።
ዩኤን ውመን ኢትዮጵያ ሁሉን አካታች እድገት እና ዘላቂ ልማትን የጀመረችውን ጉዞ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አመልክተዋል።
የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ሴሲል ሙካሩቡጋ ዩኤን ውመን ኢትዮጵያ ስርዓተ ጾታን ያማከለ የበጀት ዝግጅቷን እንድታሻሻል እና ሁሉን አካታች እድገት እንድታስመዘግብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።