ተማሪዎችን በሒሳብና እንግሊዘኛ ትምህርት ውጤታማ የሚያደርግ የቴሌቪዥን ትምህርት ስርጭት ከሰኞ ጀምሮ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ መተላለፍ ይጀምራል

You are currently viewing ተማሪዎችን በሒሳብና እንግሊዘኛ ትምህርት ውጤታማ የሚያደርግ የቴሌቪዥን ትምህርት ስርጭት ከሰኞ ጀምሮ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ መተላለፍ ይጀምራል

AMN – የካቲት 25/2017 ዓ.ም

ተማሪዎችን በሒሳብና እንግሊዘኛ ትምህርት ውጤታማ የሚያደርግ የቴሌቪዥን ትምህርት ስርጭት ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ AMN ፕላስ ቻናል መተላለፍ ይጀምራል፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ እና አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ትምህርት በቴሌቪዥን መጀመሩም ይህንኑ ጥረት ይበልጥ የሚያግዝና በሂሳብና እንግሊዘኛ ትምህርቶች ላይ የነበረውን ውስንነት ለመቅረፍ የሚረዳ ነው ብለዋል።

በቀጣይ የሚሰራጨው ትምህርት የተዘጋጀው ለተማሪዎች ለጥናት እንዲያግዝ ታስቦ በመሆኑ በቅድሚያ በመስኩ ባለሙያዎች የይዘት መረጣ እንዲከናወን ተደርጓል ያሉት ኃላፊው በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ መምህራንን አቅም በመጠቀም በተመረጡ መምህራን ቀረፃው እንዲከናወንና ለስርጭት ዝግጁ እንዲሆን ተደርጋልም ብለዋል።

ስርጭቱ ከ4ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች በ3 የማስተማሪያ ቋንቋዎች ማለትም አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ እና እንግሊዘኛ መሆኑም ተነግሯል።

በከተማዋ በትምህርት ላይ የተጀመረውን ለውጥ ለማሳካት የትውልድ ድምፅ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የራሱን ድርሻ ሲወጣ መቆየቱን የገለፁት የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ተማሪዎች በቴክኖሎጂ ታግዘው እንዲማሩ ሚናውን እየተወጣ ነው ብለዋል።

ከዚያ ባለፈ አዲስ ሚዲያ ኔተዎርክ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በኩል የትምህርት ቁሳቁስ እና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ ሰለመሆኑም ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።

የትምህርት በቴሌቪዥን ስርጭቱ ከሰኞ እስከ ዓርብ ማታ ከ11፡00 እስከ 2፡00 ሰዓት ድረስ፤ ቅዳሜና እሁድ ደግሞ ከጠዋት 2፡00 እስከ 6፡00 ሰዓት ድረስ መሆኑም ተነግሯል።

በአሰግድ ኪ/ማርያም

የ AMN plus ቻናልን በዚህ ያገኙታል:-

AMN plus on ethiosat

Frequency 10985 MHz

Pol horizontal

Symbol rate 45000

FEC 5/6

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review