የኮሪደር ልማቱ የመዝናኛ ቦታዎችን ያካተተ በመሆኑ ከከተማ ወጥቶ ልጆችን ለማዝናናት ይውል የነበረን ገንዘብ መቆጠብ እንዳስቻላቸው ወላጆች ተናግረዋል
ሰዓቱ ነፋሻማው አየር የሚነፍስበት ወደ 11፡30 ገደማ ነው፡፡ በግምት በጉልምስናው የዕድሜ እርከን ላይ ያሉ የሚመስሉት አቶ ይክፈለኝ ሞልቶለት ነፋሻማውን አየር ደረብረብ ባለው አለባበሳቸው እየመከቱ ንባባቸውን ቀጥለዋል፡፡ በተለምዶ 70 ደረጃ በመባል በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ ዋናው መንገድ በተሰራ አነስተኛ መናፈሻ አረፍ ብለው መጽሐፍ ሲያነቡ ነው ያገኘናቸው።
በመዲናዋ የኮሪደር ልማት በተከናወነባቸው መስመሮች የህጻናት መንሸራተቻ፣ ዥዋዥዌ፣ ዝላይና መሰል መጫወቻዎች እንዲሁም ማረፊያና ካፍቴሪያ የተዘጋጀባቸው በርካታ ናቸው። በአራዳ ክፍለ ከተማ ውስጥም መሠል ልማቶች በስፋት ተሰርተዋል፡፡ 70 ደረጃ አካባቢ በተሰራ አነስተኛ መናፈሻ ውስጥ ያገኘናቸው አቶ ይክፈለኝ፣ “ልጆቻችን አስታዋሽ አገኙ፡፡ ይኸው እኔም ሁለት ልጆቼን እያዝናናሁ፣ እኔም መፅሐፍ አነባለሁ” ይላሉ የአምስት እና የሶስት ዓመት ዕድሜ ወዳላቸው ልጆቻቸው ጣታቸውን ቀስረው እያመለከቱ፡፡
ከዚህ ቀደም ልጆቻቸውን ለማዝናናት ትንሽ ርቀው መጓዝ ግድ ይላቸው አንደነበርና በተለይ የአረንጓዴ ቦታዎችና ተፈጥሯዊ መልክ ያለው የመዝናኛ ቦታዎች እጥረት እንደነበር አንስተው፣ አሁን በአቅራቢያቸው እንደዚህ አየሩ ነፋሻማ ሲሆን፣ ልጆቻቸውን ለማዝናናትና በነጻነት ለመንቀሳቀስ ምቹ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች በተለይም ልጆች የልብ መሻታቸውን የሚሞሉ የመዝናኛ ቦታዎችን በቅርበት ባለማግኘታቸው ምክንያት ከከተማዋ ርቀን እንጓዝ ነበር የሚለው አስተያየት የብዙዎች ነው፡፡ የኮሪደር ልማቱ በመዲናዋ የእግረኛ እና የሳይክል መንገዶች የተለዩባቸው ጎዳናዎች በስራ ላይ ከማዋላቸው ባሻገር፣ በአጭር ጊዜ ይሰራል ተብሎ ሊገመቱ የማይችሉ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች፣ ውብ፣ ፅዱና አዲስ ገፅታ ለመፍጠር አስችሏል፡፡
ተማሪ ሀና ጋዲሳ በቀበና አካባቢ በተሰራው የኮሪደር ልማት መናፈሻ ላይ ከጓደኞቿ ጋር ስትጫወት አግኝተናታል። በፊት በፈለጉት ቦታ የመዝናኛ ቦታዎች ባለመኖሩ ከትምህርት ቤት መልስ ቤታቸው ይቀመጡ እንደነበር ትናገራለች፡፡ አሁን ግን በየመንገዱ ዳር በተሰሩት የመናፈሻ ቦታዎች እና ወንበሮች ላይ ከጓደኞቿ ጋር የመዝናናት ዕድል እንዳገኙ ገልጻለች፡፡
በትምህርት የተጨናነቀውን አእምሯቸውን በማዝናናት መንፈሳቸውን የማደስ አጋጣሚ እንደተፈጠረላት የምትናገረው ተማሪ ሀና፣ በተለይ ቀበና እና አራት ኪሎ አካባቢዎች በጣም ውብና ያማሩ ሆነው መሰራታቸው አማራጭ የመዝናኛ ስፍራዎችን እንዳሰፋ ተናግራለች፡፡
ወጣት አለማየሁ ተሰጋ በሰባ ደረጃ አካባቢ በተሰራው የመናፈሻ ቦታ ላይ ቁጭ ብሎ ሲዝናና ያገኘነው ወጣት ነው፡፡ በፊት ከተማዋ ደረጃውን የጠበቀ የእግረኛ እና የመዝናኛ ቦታ ያልነበራት ሲሆን፣ የመኪና መንገድ ላይ ሰው በመሄድ ለአደጋም ይጋለጥ ነበር፡፡ መንገዱ በሰው የተጨናነቀ እና በቆሻሻ የተሞላ መጥፎ ሽታ ነበር የሚለው ወጣት አለማየሁ፤ ልጆች ወጥተው የሚጫወቱበት፣ የሚቦርቁበት ቦታ ማግኘት ከባድ እንደነበር አስረድቷል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ብሎም በከተማ ደረጃ ለልጆችም ሆነ ለወጣቶች መዝናኛ የሚሆን ምቹ ቦታ ማግኘት ከባድ እንደነበር ይጠቅሳል፡፡ አሁን የኮሪደር ልማትን ተከትሎ የተሰራው የልጆች መጫወቻ፣ ፋውንቴንና መናፈሻ ቦታዎች መንፈስን ያድሳሉ፤ ሲመለከቷቸው ያስደስታሉ፤ ለከተማዋም ተጨማሪ ውበትን ፈጥረዋል ብሏል፡፡

በስራም ሆነ በተለያየ ነገር አእምሮ ሲወጠርና ሲጨናነቅ ወጣ ብሎ መዝናናት ጭንቀትን እንደሚያስወግድለት ወጣቱ ያስረዳል፡፡ መንግስት ለከተማዋ ውበት ትኩረት በመስጠት የመናፈሻ ቦታዎች በመገንባት ረገድ ያደረገው ነገር በጣም እንዳስደሰተው ገልጿል፡፡
ወይዘሮ ገነት ባየህ አዲስ በተሰራው የሰባ ደረጃ መናፈሻ ሁለት ልጆቻቸውን ሲያዝናኑ ያገኘናቸው እናት ናቸው። ከቤታቸው ወጣ ብለው ብዙም ሳይጉላሉ ልጆቻቸውን የሚያዝናኑበት ስፍራ ማግኘት መቻላቸው መልካም መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በአካባቢው ልጆች የሚዝናኑበት ፋውንቴን፣ አበባ እና የመናፈሻ ቦታ ባለመኖሩ የልጆች መጫወቻ ማግኘት ከባድ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህ ችግር አሁን በኮሪደር ልማቱ መቀረፉን ገልፀዋል፡፡

አቶ ታደሰ በላይ በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 6 ነዋሪ ናቸው፡፡ የኮሪደር ልማቱ ለልጆች መዝናኛ ስፍራዎችን ያካተተ መሆኑ አስደስቷቸዋል፡፡ ልጆች ወጥተው የሚጫወቱበት ቦታ እጥረት እንደነበር የሚገልጹት አቶ ታደሰ፣ አሁን የመንገዱን የግራ እና ቀኝ ጠርዝ ተከትሎ የተሰሩት የመዝናኛ ስፍራዎች መልካም ጅምሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከአሁን በፊት ልጆች በሰፈራቸው የሚዝናኑበት ቦታ ማግኘት ቀርቶ ወጥተው የሚገቡበት በቂ መንገድም እንዳልነበራቸው በዚህም በቤታቸው ተወስነው ይውሉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ቅዳሜና እሁድን ጠብቀው ወደ እንጦጦ ተራራ የሚወጡት እነ አቶ ታደሰ እና ልጆቻቸው አሁን ማታ፣ ማታ ከሰባ ደረጃ አራት ኪሎ፣ ቀበና ድረስ የእግር ጉዞ በማድረግ እየተዘዋወሩ እንደሚጎበኙ ተናግረዋል፡፡
አቶ ታደሰ እና ልጆቻቸው አካባቢያቸውን ተዟዙረው በመጎብኘት ተደስተው እንደሚመለሱ ጠቁመዋል። የኮሪደር ልማቱ የመዝናኛ ስፍራዎችን በበቂ ሁኔታ ከማግኘት አኳያ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል። የተሰሩት የመዝናኛ ቦታዎች ልጆች እና ወላጆች በጋራ ወጥተው እንዲዝናኑ አስችሏል፡፡ አሁን እነሱ የሚኖሩበት አካባቢ ውብ ከመሆኑ በላይ አዲስ አበባም ለመዝናኛ ተመራጭ ከተማ እየሆነች መጥታለች። በቀጣይም የኮሪደር ልማቱ ተደራሽ ባልሆነባቸው ቦታዎች የመዝናኛ ቦታዎች ተደራሽ ቢደረጉ የነበረውን የመዝናኛ ቦታ እጥረትን ይበልጥ እንደሚቀርፈው ጨምረው አስረድተዋል፡፡
አቶ ፋንታሁን ተገኝም የአቶ ታደሰን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ የኮሪደር ልማቱ ለክፍለ ከተማው ብሎም ለከተማዋ ልጆች የመዝናኛ ስፍራዎችን ጸጋን ይዞ እንደመጣላቸው ተናግረዋል፡፡ ልጆች መንገድ ዳር በተሰሩ ወንበሮች ላይ በማረፍ፣ ፋውንቴኖችን በመመልከት እየተዝናኑ ነው፡፡ የኮሪደር ልማቱ የነበረባቸውን የመናፈሻ ቦታዎች እጥረትን እንደቀረፈላቸው ገልጸዋል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ የወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይልማ ተረፈ ክፍለ ከተማው ነባር ከሚባሉ የከተማዋ ክፍለ ከተሞች መካከል ዋነኛው ሲሆን በርካታ ልጆችና ወጣቶች ለዘመናት የመዝናኛ ቦታዎች እጥረት ያጋጥማቸው እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
ክፍለ ከተማው እንደ ፒያሳ ዶሮ ማነቂያ፣ ሰራተኛ ሰፈር፣ አምስት ኪሎ፣ አራት ኪሎ ያሉ ነባር ሰፈሮችን እና እስከቀበና አካባቢ ድረስ በርከት ያለ የህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ጥግግት በአንድ ላይ ይኖርባቸው እንደነበር አውስተው፣ የክፍለ ከተማው ልጆች እና ወጣቶች ክፍት ቦታ ባለመኖሩ ምክንያት በብዙ አካባቢዎች ላይ የመዝናኛ ቦታ እጥረት ያጋጥማቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ ብዙ ስራዎች እንደተሰሩ የሚገልጹት አቶ ይልማ ከእነዚህ መካከል ሰፋፊ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች እና የመዝናኛ ቦታዎች ተሰርተዋል፡፡ በእነዚህ መንገዶች ህጻናት ልጆች ብስክሌት ሲነዱ እና ሲለማመዱ ይታያሉ፡፡

ወጥተው የሚዝናኑበት ቦታ የሌላቸው ብዙ የክፍለ ከተማው ልጆች አሁን መተንፈሻ ቦታ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተሰሩ የመዝናኛ ቦታዎች ላይ ቅዳሜና እሁድ ብቻ ሳይሆን በመደበኛ ቀናት በርካታ ልጆች እና ነዋሪዎች እየተዝናኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የእግረኛ መንገዶችን ተከትሎ በብዙ ቦታዎች ላይ በየ300 ሜትሩ የመናፈሻ ቦታዎች መሰራታቸውን የሚጠቁሙት ኃላፊው፣ በእነዚህ ላይ ፋውንቴኖች፣ ማንበቢያ ስፍራዎች፣ ቁጭ ብለው ሻይ ቡና የሚሉበት ማረፊያዎች፣ የመሮጫ ትራኮች፣ አነስተኛ ሜዳዎች እና የጂምናዚየም ቦታዎች መካተታቸውን ገልፀዋል፡፡ በእነዚህም በርካታ የክፍለ ከተማው ልጆች እንዲሁም ወጣቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ወጣቶች አልባሌ ቦታዎችን እንዲያዘወትሩ ከሚያስገድዷቸው በርካታ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ በቂ የመዝናኛ ስፍራ አለመኖር እንደሆነ አንስተው፣ የኮሪደር ልማቱ እነዚህን የመዝናኛ ቦታዎች እጥረትን በብዙ መልኩ መመለሱን ገልፀዋል፡፡
በይግለጡ ጓዴ