በቱሪዝም ዘርፍ የተሰሩ ልማቶች ከተማዋን ከቱሪስቶች መሸጋገሪያነት ወደ መዳረሻነት እንደቀየሯት ምሁራን ተናገሩ
አንዳንድ ሀገራት ድንቅ ናቸው፡፡ እንቁላል ብቻ ሳይሆን ወርቅ የሚጥሉ ዶሮዎች አሏቸው። እነዚህ ዶሮዎች የቱሪስት መስህቦች ይሰኛሉ፡፡ አዎ ቱሪዝም እንዲያ ነው! ይላሉ የዘርፉ ምሁራን፤ በቀላሉ ወርቅ የሚታፈስበት የኢኮኖሚ ዋልታ፡፡
ኢትዮጵያም ሚዛኗ ዝንፍ የማይለው ተፈጥሮ ያደላችላት ይመስል በቱሪዝም መስህብ ሀብቶች የተንበሸበሸች ናት ሊባል ይችላል፡፡ ብዙ ወርቅ የሚጥሉ ዶሮዎችን የታደለች ምድር፡፡ በጣም ዝቅተኛ ቦታ ከሆነውና ከሚጨሰው ‘ኤርታ አሌ’ ተነስተን በረዶ ከሚፈልቅበት እና ቀዝቃዛ ወላፈን ከሚጋረፍበት ራስ ዳሽን ተራራ እስክንዘልቅ ድረስ ኢትዮጵያ መልኳና ሀብቷ ብዙ ነው፡፡
ወደ ምስራቅ ተጉዘን ኤጀርሳ ጎሮ ተራራን እንውጣ፡፡ በዚያ በቁንዱዶ ተራራ ሰማይ ስር የሚቦሩቁትን የቁንዱዶ የዱር ፈረሶች ብንመለከት ኢትዮጵያ ምን ያህል በተፈጥሮ የታደለች ሽቅርቅር ሀገር መሆኗን እኛው ምስክር እንሆናለን፡፡
የቁንዱዶዎች ፈረሶች በኢትዮጵያ እንጂ ዓለም ላይ የትም የሉም። አንጡራ የኢትዮጵያ ሀብት ናቸው፤ እንደ ቀይ ቀበሮ፣ እንደ ዋሊያ…። ለካንስ ነገሮች ቢመቻቹላቸው በየዓመቱ ሚሊዮን ዶላሮችን ለኢትዮጵያ የሚያስገኙ ‘የጋማ ነዳጆች፣ የተራራ ወርቆች’ ናቸው። ኤጀርሳ ጎሮ ሌላ አክሱም፣ ሌላ ላል ይበላና ሌላ ኤርታ አሌ ነው።
“ቁንድዶ የሚገርም ተራራ ነው። ተራራው ጫፍ ላይ ውሃ አለ። አረንጓዴ ነው። እንደ ወንጪ ሐይቅ ነው። ተፈጥሮ ራሱ እንዴት እንደጠበቀችው…” ሲል ቢቢሲ በዘገባው ኢትዮጵያ ገና በወጉ ያልተገለጡ እና ወርቅ ሊታፈስባቸው የሚችሉ የቱሪዝም መስኮችን የታደለች ምድር መሆኗን በአድናቆት መስክሮ ግን ደግሞ ከዘርፉ በሚገባት ልክ አለመጠቀሟን የሚያስቆጭ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሆስፒታሊቲ እና የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ደመቀ ክብሩ እንደሚሉትም፣ እንደ ሀገር በቱሪዝም ዘርፍ እልፍ የሆነ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብት አለን፡፡ ይሁን እንጂ በሚገባው ልክ ገልጠን አልተጠቀምንባቸውም፡፡
ይህም ከግንዛቤ ክፍተት፣ ከትኩረት ማነስ፣ ከመዳረሻ መሰረተ ልማቶች ግንባታ እጥረት፣ ከማስተዋወቅና መሰል ክፍተቶች ምክንያት የመጣ ችግር ነው። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ቱሪዝምን እንደ አንዱ የኢኮኖሚ ዋልታ አድርጎ መንቀሳቀሱ እና ይህንንም ተከትሎ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎች እየተገነቡ በመሆኑ በዘርፉ አዳዲስ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው ብለዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ “ኢትዮጵያ ኢን ፎከስ” በተሰኘው ፕሮግራም ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ቢልለኔ ስዩም ጋር በቅርቡ ቆይታ አድርገው ነበር። ታዲያ በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያን ቱሪዝም ዘርፍ ሀገሪቷ ያላት ብዝሃነት እና የምድረ ቀደምትነት ታሪክ በጣም የተለየ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ቢሆንም በመስኩ ያለውን እምቅ አቅም ወደ ዘላቂ ተጠቃሚነት የመቀየር ተግባር በሚፈለገው ደረጃ ሳይሰራበት መቆየቱን አመልክተው፣ ከለውጡ ወዲህ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ ትኩረት በመስጠት ዘርፈ ብዙ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፣ ነባር የቱሪዝም ስፍራዎችን የማልማት፣ አዳዲስ የቱሪዝም ስፍራዎች የመገንባት፣ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር የመጨመር፣ የአሰራር ማዕቀፎች ዝግጅት እና የቱሪዝም ስፍራዎችን በተቀናጀ ሁኔታ ማስተዋወቅ ከተከናወኑ ስራዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመሩ “የገበታ ለሸገር” እና “የገበታ ለሀገር” ፕሮጀክቶች የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋት ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው።
በተለይ በመዲናዋ የሚገኙት የወዳጅነት አደባባይ፣ አንድነት ፓርክ፣ ሳይንስ ሙዚየም፣ እንጦጦ ፓርክ፣ የመስቀል አደባባይ መልሶ ግንባታ፣ አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት፣ የብሔራዊ ቤተ መንግስት ዕድሳት፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዳራሽ ዕድሳት፣
የብሔራዊ ሙዚየም ዕድሳት፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታ፣ አዲስ ዓለም አቀፍ የኮንቬንሽን ማዕከል ግንባታ እና የኮሪደር ልማትን ተከትሎ የተከናወኑ ተግባራት ከተማዋን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ እንዳደረጓት ተናግረዋል።
በተለይ የኮሪደር ልማት ስራው የአዲስ አበባን መልክ በአዲስ ሁኔታዎች በመግለጥ የጎብኚዎች ዐይን ይበልጥ እንዲያርፍባት ማድረጉን ገልፀው፣ ይህም ከተማዋን ከቱሪስቶች መሸጋገሪያነት ወደ መዳረሻነት አድርሷታል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የመንግስትና የግል ዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች የባህልና ቱሪዝም መምህርና ተመራማሪ አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ለቱሪዝም ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት እጅግ አመርቂ ነው ይላሉ። በተለይም በፖሊሲ ደረጃ ቱሪዝም እንደ አንድ የኢኮኖሚ ዋልታ ተቆጥሮ እራሱን ችሎ እንዲቆም መደረጉ ዘርፉ ያልተገደበ እድገት እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተሰሩ አዳዲስ መስህቦች ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይና መነቃቃትን የፈጠረም ነው ያሉት አያሌው (ዶ/ር)፣ “አንድ ሀገር በቱሪዝም ዘርፍ የተሻለ ነው ለመባል ምን መስህብ አለው? ጎብኝዎች ምን ያህል ጊዜ ቆዩ? ምን ያህል ገቢስ ተገኘ? የሚሉ ነጥቦች እንደ መስፈርት ይቆጠራሉ። ከእነዚህ ነጥቦች አንፃር አሁን ኢትዮጵያ መልካም የሚባል ሁኔታ ላይ ትገኛለች” ብለዋል፡፡
ጎብኚዎችን ለመሳብና የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም እንደ አዲስ አበባ ከተማ እና እንደ ሀገር እየተሰሩ ያሉ በርካታ ፓርኮች ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ እንደ አጠቃላይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የመዳረሻና የቱሪዝም መሠረተ ልማት ዕድገት ላይ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ያሉት የቱሪዝም ባለሙያው፣ አዲስ አበባም ከመሸጋገሪያነት ወደ መዳረሻነት ስለማደጓም መስክረዋል።
በርግጥ ከ2011 ዓ.ም ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማን የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ለማስፋት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። እነዚህ የልማት ሥራዎች ከተማዋ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎችን ለማከናወን ተመራጭ እንድትሆን አድርገዋታል፡፡
የባህልና ቱሪዝም መምህርና ተመራማሪ አያሌው (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ዘርፍ የተመቸች ድንቅ ሀገር መሆኗን ገልፀው፣ ይሁን እንጂ ለበርካታ ዘመናት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ያነሰ በመሆኑ ከኢኮኖሚ አንፃር ብዙም አልተጠቀመችበትም፡፡ ያለፉት ዘመናት የሚያስቆጩ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመንግስት የተሰጠው ትኩረት በተለይም እንደ አንድ ዋና የሀገር ኢኮኖሚ ዘርፍ ተደርጎ መሰራቱ ትልቅ ነገር ነው ብለዋል፡፡
አክለውም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ ልማቶች የሀገሪቱን ቱሪዝም አቅም በሚገባ የገለጡ እና ዘርፉንም የሚያሳድጉ ሀገሪቱንም በኢኮኖሚ የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በገበታ ለሸገርና ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የእንጦጦ፣ የአንድነት እና የወዳጅነት ፓርክን፣ ዓድዋ ድል መታሰቢያን የመሳሰሉት በአዲስ አበባ፤ ከአዲስ አበባ ውጪም የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት፣ የወንጪ ደንዲ ኢኮ ሪዞርት፣ በኮይሻ ፕሮጀክት የሀላላ ኬላና የዝሆን ዳና ሎጅ ፓርኮችንና ሪዞርቶች በጥራት እና በፍጥነት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል። በገበታ ለትውልድ መርሃ ግብርም በተለያዩ ክልሎች ተመሳሳይ የቱሪስት መዳረሻዎች በአማረ መልኩ እየተገነቡና የበርካቶችን ቀልብ እየሳቡ ነው፡፡
እነዚህ ልማቶች ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ አላቸው የሚሉት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሆስፒታሊቲ እና የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ደመቀ ክብሩ ለአብነትም እንደ ሀገር የ“ቤኑና መንደር”፣ የኮይሻ፣ የወንጭ እና ጎርጎራ የቱሪስት መዳረሻ እንደ ወዳጅነት፣ ዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ አንድነት ፓርክን የመሳሰሉ የቱሪስት መዳረሻዎች ሲበዙ የሀገር ኢኮኖሚ ከፍ ይላል፡፡ ሁለንተናዊ የሆነ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እና ተመራጭነትንም እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡
ከብሔራዊ ቤተ መንግስት ወይም ከአንድነት ፓርክ ተነስተን ከወንጭ እስከ ጎርጎራ፣ ከፋሲል ቤተ መንግስት እስከ ሃላላ ኬላ፣ ከእንጦጦ ፓርክ እስከ ሎጎ ሃይቅ፣ ከጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ እስከ “ቤኑና መንደር” ከፍ ብለን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተሰሩ ያሉ ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ጠቅሰን በርግጥም ከመጋቢት እስከ መጋቢት ቱሪዝሙን ከፍ ያደረጉ ስራዎች የሚያኮሩ መሆናቸውን መናገር ይቻላል ይላሉ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የቱሪዝም ባለሙያዎች፡፡
በመለሰ ተሰጋ