በአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና በፈረንሳይ ላይ ዛቻ የሰነዘረችው ኢራን፣ ሚሳኤል ማስወንጨፏን የምትቀጥል ከሆነ ትወድማለች ስትል እስራኤል አስጠንቅቃለች፡፡
አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ የቴህራንን እርምጃ ለማስቆም እስራኤልን የሚያግዙ ከሆነ፣ በቀጣናው ያሉ የጦር ሰፈሮቻቸው ላይ ጥቃት ሊሰነዘርባቸው እንደሚችል ኢራን አስጠንቅቃለች፡፡
እስራኤል የሰነዘረችውን ጥቃት ተከትሎ ኢራን የአጸፋ ምላሽ መውሰድ ጀምራለች፡፡
እስራኤል 200 ሚሳኤሎችን ያሳተፈ በአራት አቅጣጫ የመጣ ማእበል ስትል የጠራችው የኢራን የአጸፋ ምላሽን ተከትሎ፣ ሁለቱ ሀገራት የሚሰነዛዘሩት ጥቃቶች ቀጥለዋል፡፡
በዚህም የህክምና ተቋማት እንዳስታወቁት፣ በእስራኤል በኩል የ3 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካቶች ደግሞ መቁሰላቸው ተገልጿል፡፡
የኢራን የመንግስት ቴሌቪዥን እንዳስታወቀው፣ በጥቃቱ 20 ህፃናትን ጨምሮ ወደ 60 የሚጠጉ ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
ኢራን ጦርነቱን እንደምትቀጥል እና ግጭቱን በቀጣናው ወዳለው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ልታሰፋው እንደምትችል ማስጠንቀቋን ተከትሎ፣ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ቴህራን ሚሳኤል ማስወንጨፏን የምትቀጥል ከሆነ ትወድማለች ሲል አስጠንቅቋል፡፡
ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይም እስራኤልን የሚረዱ ከሆነ በቀጣናው ያለው የጦር ሰፈራቸው እና መረከቦቻቸው ኢላማ እንደሚሆኑ በቴህራን ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ሰካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡