ቻይና ከአሜሪካ በሚገቡ በአንዳንድ ሸቀጦች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ በመጣል የአጸፋ ምላሽ ሰጠች
AMN-ጥር 27/2017 ዓ.ም
ቻይና ወደ አሜሪካ በሚላኩ ሸቀጦቿ ላይ ተጨማሪ ቀረጥ መጣሉን ተከትሎ፣ በአንዳንድ ከአሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ አዲስ ቀረጥ በመጣል ፈጣን የአጸፋ ምላሽ ሰጥታለች፡፡
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በሜክሲኮ እና በካናዳ ላይ ጥለው የነበረውን ተጨማሪ ቀረጥ ያራዘሙ ሲሆን፣ በቻይና ላይ ግን እንዲፀና በማድረጋቸው፣ በሁለቱ የዓለም ታላላቅ የኢኮኖሚ ባለቤቶች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ከፍ አድርጎታል።
አደንዛዥ እፆች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የተሰራው የመከላከል ሥራ በቂ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ያስጠነቀቁት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ከዛሬ ጀምሮ ከቻይና በሚገቡ ሁሉም ሸቀጦች ላይ ተጨማሪ 10 በመቶ ቀረጥ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
ውሳኔውን ተከትሎም የቻይና ገንዘብ ሚኒስቴር በአሜሪካ የከሰል እና የተፈጥሮ ጋዝ ምርቶች ላይ 15 በመቶ፣ ለነዳጅ ዘይት፣ ለእርሻ መሣሪያዎች እና አነስተኛ ቁጥር ላላቸው የጭነት መኪናዎች እንዲሁም ከአሜሪካ ወደ ቻይና ለሚላኩ የቤት መኪናዎች 10 በመቶ ቀረጥ መጣሉን ተናግሯል።
በተጨማሪም ቻይና ፍትሃዊ የገበያ ውድድርን ከማስፈን አኳያ በጎግል ኩባንያ ላይ በዓለም አቀፉ አንቲ ሞኖፖሊ ምርመራ መጀመሯን ሚኒስቴሩ አያይዞ ገልጿል፡፡
በተለየ መልኩ የቻይና የንግድ ሚኒስቴር እና የጉምሩክ አስተዳደር ለኤሌክትሮኒክስ፣ ለወታደራዊ መሳሪያዎች እና ለሶላር ፓኔሎች ወሳኝ የሆኑ ማዕድናት ወደ ውጭ እንዳይላኩ ቁጥጥር እያደረጉ ስለመሆናቸው መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ቻይና ከአሜሪካ በሚገቡ በአንዳንድ ሸቀጦች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ በመጣል የአጸፋ ምላሽ ሰጠች
