AMN – ታኅሣሥ 21/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ የተለያየ እምነት፣ ቋንቋዎች እና ብዝኃ ማንነቶች የሚንጸባረቁባት የኢትዮጵያ ማሳያ እንደመሆኗ ኅብረ ብሔራዊዋን ከተማ የሚመጥን ሚዲያ እየተገነባ ነው ሲሉ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሣሁን ጎንፋ ገለጹ።
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ኤ ኤም ኤን ፕላስ (AMN PLUS) በሚል የሰየመው ተጨማሪ የቋንቋዎች ቻናል መደበኛ ሥርጭቱን በይፋ ጀምሯል።
በመደበኛ ሥርጭት ማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ ንግግር ያደረጉት አቶ ካሣሁን ጎንፋ፣ አዲስ አበባ የተለያዩ እምነቶች፣ ቋንቋዎች እና ብዝኃ ማንነቶች የሚንጸባረቁባት የኢትዮጵያ ማሳያ መሆኗን ተናግረዋል።
በመሆኑም በከተማዋ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች በከተማዋ የሚከናወኑ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በቋንቋቸው ተደራሽ ማድረግ ያለመ ተጨማሪ ቻናል መክፈት ማስፈለጉን አንሥተዋል።
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የሚያዳምጡት እና የሚያዩት ብቻ ሳይሆን የሚናገሩበት ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ጭምር መረጃዎችን በማሠራጨትም ኢትዮጵያን ከፍ አድርጎ ለብዙኃኑ ለማሳየት ይሠራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ መዲና እና የዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ ትልቅ ከተማ እንደመሆኗ ከተማዋን የሚመጥን ብዙኃን መገናኛ እንደሚያስፈልጋትም ነው ያነሡት።
በዚህም አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በዋና የቴሌቪዥን ቻናሉ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ የአፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛ፣ ሶማሊኛ፣ የእንግሊዝኛ እና የዓረብኛ ቋንቋ ዝግጅቶችን ሲያቀርብ መቆየቱን አቶ ካሣሁን አስታውሰዋል።
እነዚህ ዝግጅቶቹም ከዛሬ ጀምሮ ኤኤምኤን ፕላስ (AMN PLUS) በተሰኘ ቻናሉ ራሳቸውን ችለው ሰፊ የአየር ሰዓት ይዘው መሠራጨት መጀመራቸውንም አብስረዋል።
በታምራት ቢሻው