AMN – የካቲት 30/2017 ዓ.ም
ነገአችንን የምንገነባው ባህልና ወጎቻችንን በአግባቡ መንከባከብና ማጎልበት ስንችል ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።
ከየካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ሁነቶች ሲካሄድ የቆየው የ72ኛው ዙር የቦረና አባ ገዳ ባሊ (ሥልጣን) ርክክብ በምሥራቅ ቦረና ዞን አሬሮ ወረዳ አርዳ ጂላ በዳሳ ተካሂዷል።
በዚህም የ71ኛው ዙር አባ ገዳ ኩራ ጃርሶ ለ72ኛው አባ ገዳ ጉዮ ቦሩ ጉዮ ሥልጣናቸውን ባማረ መልኩ አስረክበዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት መልዕክት የገዳ ሥርዓት በህዝቡ ባህልና እሴቶች ታንፆ እና በሂደት ያጋጠሙ ችግሮች በጥናት በማስተካከል እዚህ ደርሷል።
“ነገአችንን የምንገነባው ባህልና ወጎቻችንን በአግባቡ መንከባከብና ማጎልበት ስንችል ነው” ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ትውልዱ ዘመኑን በዋጀ ሁኔታ ወጉንና ባህሉን በማደስ አጎልብቶ ማስቀጠል ይገባዋል ብለዋል።
“የክልሉ መንግሥትም ይኸን መሠረት በማድረግ በሥርዓተ ትምህርትና በቴክኖሎጂ ግንባታ እንዲሁም በማህበራዊውና ኢኮኖሚያዊ ልማት ሂደት ውስጥ የህዝቡን ባህልና ወግ መሠረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል” ብለዋል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ በበኩላቸው “የገዳ ሥርዓት በዘመናት የስልጣኔ ሂደት ሁሉ ራሱን እያደሰ እና ፈተናዎችን እያለፈ ባማረ መልኩ ለዚሀ በቅቷል” ብለዋል።
“ቦረና ገዳን እንደ ልጁ ተንከባክቦ ለዚህ አድርሷል” ያሉት ሃላፊዋ፤ “የገዳ ሥርዓት ትውልድን እየገነባ ያስቀጠለ በመሆኑ ለወፊቱም አምሮና ጎልብቶ ይቀጥላል” ብለዋል።
የክልሉ መንግሥትም የገዳን ሥርዓት ትውልዱ እንዲማረውና ለዓለም እንዲተዋወቅ አጠናክሮ ይሰራል ሲሉ አስታውቀዋል።
በመርሃ ግብሩ የኬንያ ልዑካን ቡድን የተሳተፉ ሲሆን በኬንያ የማርሳቤት ካውንቲ ገዥ መሐሙድ ዓሊ ባስተላለፉት መልዕክት “የዛሬው እለት የደስታ ቀን ነው፤ እኛም የወንድሞቻችንን ደስታ ለመካፈል መጥተናል” ብለዋል።
“የገዳ ሥርዓት ውብ ባህልና ጥንታዊ የዴሞኪራሲ ሥርዓት ነው” ያሉት ገዥው፤ ይኸንን ውብ ባህል ጠብቀው ያቆዩትን አካላት አመስግነዋል።
ገዥው በስነ ስርአቱ ላይ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶን የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክትንም አስተላልፈዋል።

የምሥራቅ ቦረና ዋና አስተዳደሪ አቶ አብዱረዛቅ ሁሴንና የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱሰላም ዋሪዮም የቦረና ህዝብ የገዳ ሥርዓት እሴቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ያስቻለ ህዝብ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ዛሬ ሥልጣናቸውን የተረከቡት 72ኛው የቦረና አባ ገዳ ጉዮ ቦሩ ጉዮም ለሚቀጥሉት ስምንት ዓመታት የገዳውን ስርዓት በበላይነት ይመራሉ።