ንብረትነቱ የአራዳ ክፍለ ከተማ የፅዳት አስተዳደር የሆነ የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ የሰረቀ ተከሳሽ በ6 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት ተቀጣ

You are currently viewing ንብረትነቱ የአራዳ ክፍለ ከተማ የፅዳት አስተዳደር የሆነ የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ የሰረቀ ተከሳሽ በ6 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት ተቀጣ

AMN – የካቲት 26/2017 ዓ.ም

ንብረትነቱ የአራዳ ክፍለ ከተማ የፅዳት አስተዳደር የሆነውን የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ የሰረቀ ተከሳሽ በ6 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት መቀጣቱን የአራዳ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል፡፡

ተከሳሽ እስራኤል ይስሀቅ ወንጀሉን የፈፀመው ነሐሴ 24 ቀን 2016 ዓ/ም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ከሌሊቱ 6፡40 ሰዓት ገደማ ነው፡፡

ተከሳሽ ንብረትነታቸው የአራዳ ክፍለ ከተማ የፅዳት አስተዳደር ፅህፈት ቤት የሆነና ለኮሪደር ልማት አገልግሎት የዋሉ፤ በመንገድ ላይ የተተከሉ ብዛታቸው 9 የሆነ የአንዱ ዋጋ ግምት 33ሺ 28 ብር አጠቃላይ ግምቱ 297ሺህ 252 ብር የሚያወጣ የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ከሌሊቱ ሰርቆ ለማምለጥ ሲሞክር በወንጀል መከላከል ስራ ላይ ተሰማርተው በነበሩ የፖሊስ አባላት እጅ ከፍንጅ ሊያዝ መቻሉን የወንጀል ምርመራ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

ፖሊስ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማደራጀት በአቃቤ ህግ በኩል ክስ እንዲመሰረትበት ማድረጉን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በፖሊስ በኩል ምርመራው በበቂ ማስረጃ የተጣራውን እና በአቃቤ ህግ የተዘጋጀውን የክስ መዝገብ ሲከታተል የቆየው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አምስተኛ ወንጀል ችሎት፣ ተከሳሽ እስራኤል ይስሀቅን በ6 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፎበታል።

ለነዋሪው ዕለታዊ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ለአካባቢው ውበት የሆኑ የህዝብ ንብረቶች ላይ የሚፈፀሙ ህገ ወጥ ድርጊቶችን በመጠቆም ረገድ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጎን በመሆን በመጠበቅ፣ በመከባከብ እና ሥርቆት እንዳይፈፀምባቸው በመከላከል የተለመደውን ትብብር ሊያጠናክር እንደሚገባም የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review