አሰባሳቢው መድረክ – ኢሬቻ

መስከረም ሰፊ ታሪክ ያለው ልዩ ወር ነው፡፡ የተለያዩ ህዝባዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው በዓላት በስፋት ይከበሩበታል። የኢትዮጵያ የብዝሃ ባህል ሀብቶች በአደባባይ ይታዩበታል:: በዚህ ወቅት ከሚከበሩ በዓላት መካከል ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ኢሬቻ አንዱ ነው፡፡

ኢሬቻ በዓመት ሁለት ጊዜ ይከበራል። አንደኛው ከመስከረም ወር አጋማሽ በኋላ የሚከበረው ኢሬቻ መልካ ሲሆን፤ ሌላኛው የበጋው ወራት ተገባዶ በልግ ሲገባ፣ ግንቦት ወር ተራራ ላይ በመውጣት የሚከበረው ኢሬቻ ቱሉ ነው፡፡ 

በዛሬው ዕለት ከተለያዩ የሀገሪቱ ማዕዘናት የሚኖሩ የኦሮሞና የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ በውጭ ሀገራት ጭምር የሚኖሩ ሰዎች ተሰባስበው መሬ ሆ … መሬ ሆ… (ዞሮ መጣልን) እያሉ ፈጣሪን የሚያመሰግኑ ዜማዎችን እየዘመሩ፣ ሳርና አደይ አበባ በመያዝ  ወደ መልካ (ወንዝ) በመውረድ ፈጣሪን ያመሰግናሉ፡፡ በታላቅ ድምቀት በሚከበረው ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በርካታ ሰዎች በህብረ ቀለማዊ አልባሳት ተውበውና አጊጠው በዓሉ ላይ ይሳተፋሉ፡፡

በሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ ሲከበር

ወጣት ሰይድ ስሜ በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ አካባቢ ነዋሪ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ መሳተፍ ከጀመረ አምስት ዓመት ሆኖታል፡፡ በመጀመሪያ በኦሮሞ ብሔር ወንድሞቹ ግብዣ ቀርቦለት ነበር  የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል ላይ የተሳተፈው፡፡ “እውነቱን ለመናገር ከመሳተፌ በፊት የኢሬቻ በዓልን አላውቀውም ነበር፡፡ በበዓሉ ላይ የሚታየው ደስታ፣ ሰላምና አንድነት ነው፡፡ ከወንድሞቼ ጋር አብሬ በዓልን በማክበሬ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ስለበዓሉ የነበረኝን ግንዛቤ አሳድጎልኛል፤ ሀገራችን በርካታ ውብ በዓላት ያላት መሆኗን እንድረዳና እንድኮራ ነው ያደረገኝ፡፡” ይላል፡፡

ወጣት ሰይድ በወላይታ ባህል እንደ ሱሪ የሚለበሰውን ሓድያ እና በጥቁር፣ ቀይና ቢጫ ቀለማት የተሸመነውን ዱንጉዛውን ከላይ ደርቦ፣ በራሱ ቀለም አምሮና ተውቦ ነው ኢሬቻ ላይ የተሳተፈው፡፡ በበዓሉ ከጅማ፣ ሐረር፣ አርሲ፣ ወለጋ፣ ቦረና እና ሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች ተሳታፊዎች የሚለብሷቸው ህብረ ቀለማዊ አልባሳት፣ ባህላዊ ጨዋታዎች፣ በወንዝ ዳርቻ በመሄድ በሳር ውሃ በመረጫጨት ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበትና እርስ በርስ ይቅር የሚባልበት ክንውን ልዩ የመደነቅ ስሜትን እንደፈጠረበትና እንደማረከው ይናገራል፡፡   

“እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች እርስ በርስ የምንተዋወቅባቸው ናቸው፡፡” የሚለው ወጣት ሰይድ ከፒያሳ ኢሬቻው ወደሚከናወንበት ቦታ ሲሄድ የተለያዩ ሰዎችን ተዋውቋል፤ አብሮ ፎቶ ተነስቷል፤ ትውውቃቸው እና  ወዳጅነታቸው ከበዓሉ ባሻገር የቀጠለበት ሁኔታ እንዳለም ያስረዳል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ተሳስረውና ተያይዘው በአብሮነት የኖሩ ህዝቦች ናቸው፡፡ አሁን ላይ በጥቃቅን ጉዳዮች ሊከፋፍሉን የሚሞክሩትን ጆሮ ባለመስጠት፣ እርስ በርስ መተሳሰብ፣ መተጋገዝና በአንድነት መቆም አለብን፡፡ የእጅ ጣቶቻችን ሁሉም ያስፈልጉናል፤ አንዱ ከአንዱ አይበልጥም፤ የሁሉም ጣቶች መኖር ጠንካራ ያደርገናል፡፡ ልክ እንደ የእጅ ጣቶቻችን እርስ በርስ ብንከባበር፣ ብንተባበርና በአንድነት ብንቆም ጠንካራ ኢትዮጵያን መፍጠር ቀላል እንደሆነ ወጣት ሰይድ ይናገራል፡፡

ወጣት ሰይድ በተወለደበት አካባቢ ወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል ለሆነው ጊፋታ ልዩ ስሜት አለው፡፡ የዘንድሮ የጊፋታ በዓል መስከረም 12 ቀን በወላይታ ሶዶ ሲከበር አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ፎሌዎች ስጦታ ይዘው መሳተፋቸውንና “እንኳን አደረሳችሁ” መልእክት ያስተላለፉበት እንደነበር ያነሳል፡፡ እንደ ወላይታ በሆራ ፊንፊኔና ሆራ ሀርሰዴ ኢሬቻ በዓል ላይ እንዲገኙ ግብዣ መቅረቡንና እሱን ጨምሮ የወላይታ ብሔር ተወላጆች በዘንድሮው ዓመት በሚከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ለመሳተፍ በጉጉት እየጠበቁ እንደሚገኙ አስረድቷል፡፡

“እኔ ከበፊትም ጀምሮ ኢሬቻ ላይ ስሳተፍ ነበር፤ በዘንድሮው ዓመትም በራሴ አልባሳት ተውቤ እሳተፋለሁ” የሚለው ወጣት ሰይድ፣ እንደ እንቁጣጣሽ፣ ኢሬቻ፣ ጊፋታ፣ ያሆዴ፣ መውሊድ፣ መስቀል ያሉ የዘመን መለወጫ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት የአንድነታችን ማጠናከሪያ ገመድና ጌጣችን ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ባህልም ሆነ ቋንቋ የጋራ ሀብታችን ናቸው፤ እንደ ራሳችን አድርገን ማየት አለብን ሲል ሀሳቡን አጋርቶናል፡፡

አቶ እሸቱ አዱኛ አስኮ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ የኢሬቻ በዓል በጉጉት የሚጠብቁት በዓል እንደሆነና ለረጅም ዓመታትም በቢሾፍቱ የሆራ ሀርሰዴ በዓል ላይ ሲሳተፉ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ በዓሉ ላይ ለመሳተፍ አስቀድመው ለትራንስፖርት፣ ለምግብና ለአልባሳት መግዣ የሚሆን ገንዘብ ይቆጥባሉ፡፡ ብዙውን ጊዜም በቡድን በመሆን መኪናና ምግብ በመያዝ ተመሳሳይ ቀለምና ዲዛይን ባላቸው ባህላዊ አልባሳት ተውበውና ደምቀው ነው በበዓሉ የሚሳተፉት፡፡ 

ኢሬቻ ከመጀመሪያውም አብሮነት፣ አንድነትና ፍቅር የሚታይበት በዓል ነው፡፡ ከአገኘነው ሰው ጋር በፍቅር ተጫውተንና በልተን የምናሳልፍበት፣ ከዓመት ወደ ዓመት ላሸጋገረን ፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት፣ ያለ እምነት፣ ዘር፣ ፆታና ሌሎች ልዩነቶች ሁሉም የሚሳተፍበት፣ ሰዎች የሚገናኙበት በዓል ነው፡፡ አንዱ ቢደክም፣ ቢወድቅ፣ ሌላው የሚደግፍበትና የሚያነሳበት እርስ በርስ የምንደጋገፍበትም ነው ይላሉ፡፡

አቶ እሸቱ፣ ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል ላይ ደጋግመው ተሳትፈዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓሉ ሲከበር ህፃናት ልጆቻቸውን ይዘው ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በፊት ይኖሩ ከነበሩበት ከቡራዩ ተነስተው እስከ በዓሉ በሚከበርበት ቦታ ድረስ በእግር ጉዞ በማድረግ ያከበሩበትን አጋጣሚ አይረሱትም፡፡

ከተለያዩ ብዙ ጊዜ የሆኑ ጓደኞቻቸው እና አዳዲስ ሰዎች ጋር ለመገናኘት ዕድል የሚፈጠርላቸው መሆኑ በዓሉ ትልቅ ደስታ እንደሚፈጥርላቸው ይናገራሉ፡፡ ካለው የደስታ ስሜት የተነሳ ረጅም የእግር ጉዞ አድርገው እንኳን ድካም የሚባል ነገር እንደማይሰማቸውና የሆራ ፊንፊኔ በዓልን አክብረው በነጋታው ሆራ አርሰዴ ላይ ለመሳተፍ ወደ ቢሾፍቱ እንደሚሄዱ ተናግረዋል፡፡፡

አቶ እሸቱ፣ ኢሬቻ ኦሮሞን ጨምሮ ከተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር እንዲተዋወቁ ዕድል እንደፈጠረላቸው ያነሳሉ። “የማላገኛቸውንና ባህላቸውን የማላውቀውን እንዳውቅ አድርጎኛል፡፡ ለምሳሌ ባሌ፣ ቦረና፣ ሐረሪ አካባቢ ሄጄ አላውቅም፡፡ በበዓሉ ከሁሉም አካባቢ የሚመጡ ተሳታፊዎችን ሳገኝ አጨፋፈራቸውን፣ አለባበሳቸውን፣ ባህላቸውን እያወቅኩ፣ አብረን ስንጫወት አንድነቱና መዋደዱ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በዓመት አንድ ቀን ሁሌም ከማላገኛቸው ሰዎች ጋር መጫወት ያስደስታል፡፡

ለምሳሌ በኢሬቻ በዓል ላይ የሲዳማ ብሔር ተወላጆች በራሳቸው ቀለምና አለባበስ ተውበው በዓሉ ላይ ሲሳተፉ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ እኔም ፊቼ ጨምበላላ ላይ ተገኝቼ እንድሳተፍ የሚያነሳሳ፣ ለእነሱ ያለኝ አክብሮት እንዲጨምር ነው ያደረገኝ” ብለዋል፡፡

ኢሬቻ ላይ የተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቢሳተፉ ምንም የሚከለክለው ነገር እንደሌለ የሚያነሱት አቶ እሸቱ፣ በዓላት የአብሮነታችን መገለጫዎች ናቸው፡፡ አብሮነታችንና አንድነታችን እንዲጠናከር አንዱ የሌላውን ባህል ማክበር ያስፈልጋል፡፡ በእንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች እርስ በርስ ለመተዋወቅ በር የሚከፍቱና በመካከላችን ያለው አንድነትና ፍቅር ለማጠናከር የሚረዱ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ፀሐይ ተሾመ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ነዋሪ ናት። የወጣት ፀሐይ ቤተሰብ ህብረ ብሔራዊነት የሚታይበት ነው፡፡ አባቷ የኦሮሞ፤ እናቷ ደግሞ የአማራ ብሔር ተወላጆች ናቸው፡፡ በልጅነቷም እናቷ በተወለዱበት አካባቢ በመሄድ በድምቀት የሚከበረውን የአሸንዳ በዓል ላይ ወገቧ ላይ የአሸንዳ ቅጠል በማሰርእየጨፈረች ማክበሯን ታስታውሳለች፡፡ በአዲስ አበባም በተለያዩ ጊዜያት የአሸንዳ በዓል ላይ ተሳትፋ ታውቃለች፡፡

ኢሬቻን በቢሾፍቱ ሆራ ሀርሰዴም እየተገኘች ስታከብር መቆየቷን የምትናገረው ወጣት ፀሐይ፣ በዓሉ  ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት፣ አብሮነትና አንድነት የሚታይበት እንደሆነ ትናገራለች፡፡

በሆራ ፊንፊኔ ላይም በተለያየ ዓመት የጉጂ፣ ቦረና፣ ከሚሴና ሌሎች አካባቢዎች ባህላዊ አልባሳት በመዋብ ስታከብር ነው የቆየችው። “የእኛ ቤት ኢትዮጵያን ነው የምትመስለው። በአባቴም ሆነ በእናቴ የሚከበሩ በዓላትን በድምቀት አከብራለሁ፤ በሌላው ማህበረሰብ በዓላት ላይም እሳተፋለሁ፡፡ በዚህም አንድነትን፣ መተሳሰብን፣ ፍቅርን ነው ያየሁት፡፡ ከተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች፣ የእምነት ተከታዮች፣ ከተለያዩ ሀገራት ከመጡ ነዋሪዎች ጋር እንድተዋወቅ ዕድል ፈጥሮልኛል፤ ባህላችን ውብ እንደሆነ ተረድቼበታለሁ” ትላለች፡፡

“በዘንድሮው ዓመትም ኢሬቻ በዓል ላይ ባህላዊ አልባሳትን በመልበስ ተውቤና ደምቄ ለመሳተፍ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ከቡራዩ፣ ሱሉልታ፣ ቢሾፍቱና ሌሎች አካባቢዎች ካሉ በበዓሉ አጋጣሚ ከተዋወቀቻቸው ጓደኞች ጋርም አብሬ አሳልፋለሁ” ስትል ነግራለች፡፡

ፊሌ ጃለታ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው፡፡ ባህል አንድ ማህበረሰብ ማንነቱን፣ እሴቱን፣ አስተሳሰቡን፣ ሀዘንና ደስታውን በክዋኔ፣ ዜማ፣ በቁሳቁስና ሌሎች መንገዶች የሚገልፅበት መሳሪያ ነው፡፡ ባህል የአንድ ማህበረሰብ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች መገለጫ ነው፡፡ ባህል በይበልጥ ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

የኢሬቻ በዓል በመሰረቱ የኦሮሞ ህዝብ ባህል ይሁን እንጂ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ዕድሜ፣ የኑሮ ደረጃ  ሳይለይ የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ፣ ከኢትዮጵያ ውጭም በምስራቅ አፍሪካ በሚኖሩ ህዝቦች ዘንድም ይከበራል። አንድ ሰው በኢሬቻ በዓል ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ካለው ከመሳተፍ ምንም የሚከለክለው ነገር የለም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ የትኛውንም እንግዳ ተቀብሎ በእንክብካቤ ያስተናግዳል፡፡ ኢሬቻ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያለው፣ የተለያየ እምነት ተከታይ፣ ሴት ወይም ወንድ፣ ህፃን ወይም አዋቂ ሳይል ሁሉም የሚሳተፍበት በዓል ነው፡፡

የኢሬቻ ማህበራዊ እሴት መከባበር ነው። ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን፣ ሴቶች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡ በመከባበርና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ፣ መለያየትን ሳይሆን አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ፣ የፈጣሪን ትዕዛዝ ባከበረ መልኩ የሚከበር ነው፡፡

ኢሬቻ በህዝቦች መካከል ትስስርና ማህበራዊ መስተጋብር የሚጠናከርበት በዓል ነው፡፡ በተለይ ከአምስት ዓመት ወዲህ በሆራ ፊንፊኔ የተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች፣ በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ከጎረቤት ሀገር ከኬንያ ድረስ ተሳታፊዎች እየመጡ እያከበሩት መሆኑ ለዚህ ማሳያ እንደሆነ ፊሊ (ዶ/ር) ያነሳሉ፡፡

ብዙ ጊዜ የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ፊቼ ጨምበላላ ሲከበር አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቂዎች፣ ወጣቶች እየተጋበዙ ወደ ሀዋሳ እየሄዱ ይሳተፋሉ፡፡ ኢሬቻ ላይም የሲዳማ ብሔር ተወላጆች በተመሳሳይ ተገኝተው ያከብራሉ፡፡ የከምባታ፣ ሀዲያ፣ ወላይታ፣ ጉራጌና ሌሎችም ብሔሮችና ብሔረሰቦች በቡድን ሰብሰብ ብለው በየራሳቸው ባህላዊ አልባሳት ተውበው፤ መገልገያ ቁሳቁሶችን ይዘው በመምጣት ኢሬቻን ያደምቃሉ፤ ያስውባሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ግንኙነቶች በህዝቦች መካከል ያለው ማህበራዊ ትስስርና መስተጋብር እየተጠናከረ እንዲሄድ ያግዛል፡፡

የፎክሎር ምሁሩ ፊሊ (ዶ/ር) እንደሚገልፁት፣ በኢሬቻ በዓል በህዝቦች መካከል ያለው ማህበራዊ ትስስር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ በበዓሉ አጋጣሚ የሚገናኙ የተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የባህል መሪዎችና ሽማግሌዎች ስልክ ተለዋውጠው እርስ በርሳቸው በበዓላቱ ዙሪያ ልምድ ይለዋወጣሉ፡፡ በበዓላት ላይ ተዋውቀው እስከ ጋብቻ የደረሱም አሉ፡፡ ከአንድ አካባቢ የሚመጡ ተሳታፊዎች የጉጂ፣ ቦረና፣ የሜጫ፣ ቱለማ፣ ራያ አዘቦ ወይም ሌላ ማህበረሰብ የባህል አልባሳትን ገዝተው ይሄዳሉ። የኢሬቻ ብቻ ሳይሆን የገዳ መገለጫ የሆኑትን እንደ ቦኮ፣ ሸረሮ፣ ጨሌ፣ ኢሌላ ገዝተው ይሄዳሉ፡፡

የኦሮሞ ተወላጆችም በተመሳሳይ ፊቼ ጨምበላላ ላይ ሲሳተፉ የሲዳማ መገለጫ የሆኑ ቁሳቁሶችን ይሸምታሉ፡፡ በዚህም እርስ በርስ ልምድ እና የጥበብ ዲዛይን ይለዋወጣሉ። ወጣቱ ትውልድም ከዚህ ተምሮ ትውፊቱን ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዲያሸጋግረው ይረዳል። ቁሳቁሶችን መለዋወጥ ግንኙነትን ያጠናክራል። ሌሎችም ባህላዊ መገለጫዎች ከፍተኛ ዋጋና ትርጉም ያላቸው ናቸው፡፡ በዚህ መንገድ እርስ በርስ ይማማራሉ፤ ግንኙነታቸውም እየጠነከረ ይሄዳል።

በበዓላት የሚደረጉ ግንኙነቶች ለሀገር ግንባታ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ያነሱት ፊሊ (ዶ/ር) ኢሬቻ በአንድ ቦታ በአደባባይ ብዙ ህዝብ በሚሳተፍበት ትልቅ በዓል እንደመሆኑ እሴቱ ተጠብቆ እንዲሄድ ማድረግ ይገባል። በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ላይ እንዲገባ ተደርጎ ቢከበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመታወቅና የተሻለ ቱሪስቶችን ለመሳብ  ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርም አብራርተዋል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review