የኪነ ጥበብ ሥራዎች ማህበረሰብን በማቀራረብ፣ አብሮነትን በማጎልበትና ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና አላቸው፡፡ በቋንቋና በባህል የሚለያዩ ሰዎች በኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች አማካኝነት ወደ አንድነት ይመጣሉ፡፡ በአንዱ ሃገር የተሰራ ፊልም፣ የተቀነቀነ ሙዚቃ፣ የተደረሰ ድርሰትና የተሳለ ስዕል በሌሎች ሃገራት የጥበብ ወዳጆች ዘንድ ተወዳጅነት የማግኘቱ አንዱ ምክንያት ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች በባህሪያቸው ዓለም አቀፋዊ በመሆናቸው ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍም በየዓመቱ ከታህሳስ 20 ጀምሮ እስከ ወሩ ማብቂያ ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ የሚውለው ዓለም አቀፍ የሰዋዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ቀንን መነሻ በማድረግ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን አጉልተው በሚያሳዩ የጥበብ ስራዎች ላይ አጭር ዳሰሳ አድርገናል፡፡
![](https://www.amn.gov.et/wp-content/uploads/2024/12/5ሀ-1.jpg)
ሰዋዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት በጨረፍታ
ዓለም አቀፍ የሰዋዊ ወንድማማችነት እና አህትማማችነት ቀንን መነሻ በማድረግ፣ ዩኔስኮ በይፋዊ ገጸ-ድሩ ባስነበበው ጽሑፍ “ሰዎች በተፈጥሮ የተለያዩ ናቸው፤ አብሮነት ግን በሁሉም የዓለም ክፍሎች ውስጥ ያሉ በጋራ የሚኖሩ ማህበረሰቦችን በአንድነት አስተሳስሮ የሚያኖር ነው” ይላል፡፡
አብሮነት ከዓለም አቀፍ ግንኙነቶች መሠረታዊ እሴቶች አንዱ እንደሆነ የሚያትተው የዩኔስኮ መረጃ፣ ድህነትን ለመዋጋትና የአብሮነት ባህልን ለማሳደግ እንዲሁም እርስ በእርስ መደጋገፍ አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ያትታል።
አብሮነትን የሚያሳዩ በርካታ የኪነ ጥበብ ሥራዎች እንዳሉ የጠቀሰው የዩኔስኮ መረጃ፣ ጥበብ ማህበረሰብንና ሀገርን በማስተሳሰር ረገድ ቁልፍ ሚና አለው፡፡ ማህበራዊ መስተጋብርን ከፍ ያደርጋል፡፡ በአካል የማይገናኙ ሰዎችን ያቀራርባል፡፡ በጋራ የሚኖሩ ሰዎችን ቀናነትና መተሳሰብ ያጎላል፡፡ ከልዩነቶች በላይ የሆኑ ግንኙነቶች እህትማማችነት እና ወንድማማችነትን ይፈጥራል።
ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን አጉልተው የሚያሳዩ የጥበብ ሥራዎች ሲቃኙ
የኪነ ጥበብ ስራዎች፣ ሰዎች ከራሳቸው ባህልና ቋንቋ ውጪ ያለውን ማንነትና አመለካከት እንዲረዱ ያደርጋል፡፡ ከሌሎች ሰዎች እና ሃሳቦች ጋር ፊት ለፊት ያገናኛል፡፡ ይሄ ደግሞ ሰዎች ዓለምን ከራሳቸው ባህል ውጪ ማየት እንዲማሩ እና አብሮነትን እንዲያጠናክሩ ያደርጋል፡፡
ኪነ ጥበብ ደግሞ ከተለያዩ ባህሎች የመጡ ሰዎች በሙዚቃዎች፣ በፊልሞች፣ ስዕሎች እና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች አማካኝነት እርስ በእርስ እንዲግባቡ እና እንዲረዳዱ ያግዛል። ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች እና ባህሎች ጋር የሚዛመዱት እና የሚተዋወቁት አንድም በኪነ ጥበብ ነው። በዚህ ምክንያት አንዱ የሌላውን ባህልና ዕሴት ክብር በመስጠት የጥበብ ስራው አካል ስለሚያደርገው ወንድማማችነትና እህትማማችነትን እንዲጎለብት ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡
ዘ ዴይሊ ጋርድያን “The Impact of Art on Society” በሚል ርዕስ በወርሃ ሃምሌ 2023 ባስነበበው ጽሑፍ፣ ጥበብ ከጥንት ጀምሮ የሰው ልጅ የሥልጣኔ ዋና አካል ሆኖ የኖረ፣ የመግባቢያ እና የማሰቢያ ዘዴ ሆኖ ያገለገለ የሰው ልጆች ባለውለታ ነው። ከጥንታዊ የዋሻ ሥዕሎች እስከ ብሉይ (ክላሲክ) የሆኑ ድንቅ የፈጠራ ሥራዎች፣ እንዲሁም አሁን እየኖርንበት ባለው የዲጂታል ዓለም ጭምር የጥበብ ሥራዎች ወንድማማችነትና አብሮነትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ገጸ-ድሩ አስነብቧል።
ከውበት ማራኪነቱ ባሻገር፣ ኪነ ጥበብ በህብረተሰቡ ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር እና አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ ኃይል አለው። ጥበብ ባህልን የሚቀርጽ፣ ህብረተሰቡን የሚሄስ እና ማህበረሰባዊ እሳቤዎችን በማጎልበት በኩል አይተኬ ሚና አለው ይላል፤ የዘ ዴይሊ ጋርድያን መረጃ፡፡
መምህርና የኪነ ጥበብ ሥራዎች ሃያሲ ገዛኸኝ ድሪባ ጥበባዊ ስራዎችና ወንድማማችነት እና አህትማማችነት ምን አይነት ትስስር አላቸው? በሚል ከዝግጅት ክፍላችን ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ፣ “ከኪነ ጥበብ ቀዳሚ ሚናዎች አንዱ ማህበረሰቡን ያስተሳሰሩ የአብሮነት እሴቶችን ማጉላትና መሄስ ነው፡፡ ኪነ ጥበብ የአንድን ማህበረሰብ እሴቶች፣ እምነቶች እና ዓላማዎችን አጉልቶ ያንጸባርቃል” ሲል አጫውቶናል፡፡
የኪነ ጥበብ ስራዎች የጊዜና የስፍራን ህግ በመሻር የተለያዩ ዘመናት ባህሎችና ማህበረሰባዊ ልምዶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ የማድረግ አቅም አላቸው የሚለው መምህርና ሃያሲ ገዛኸኝ፣ ይህም የጋራ ቅርሶቻችንን እንድንረዳ እና እንድናደንቅ ዕድል ይሰጠናል። በትውልዶች መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ ታሪኮችን፣ ወጎችን እና ዕውቀትን ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላው በማሻገር አብሮነትን ያጠናክራል፡፡ በዚህ መንገድ ኪነ ጥበብ የአንድን ማህበረሰብ ማንነት ለመጠበቅ እና ለመቅረጽ ሚናው እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በሃገራችን የተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ውስጥ ወንድማማችነት እና እህትማማችነትን እንዲሁም አብሮነትን የሚያጎሉ ሥራዎች በጥበብ ሰዎች ተከይነዋል፡፡ በተለይ በሙዚቃ፣ በግጥምና በፊልም የጥበብ ሥራዎች አብሮነትንና ወንድማማችነትን በማንጸባረቅ ህብረ-ባህላዊነትን በስፋት አንጸባርቀዋል፡፡ የዛለውን አጽናንተዋል። የደከመውን አበርትተዋል፡፡ የዕውቁ ሙዚቀኛ ቴዎድሮስ ታደሰ ዝምታ የተሰኘ ሙዚቃ ለዚህ ጥሩ አስረጅ ነው፤
ያሰብከው ባይሞላም
ያልከው ባይሳካም…
ያለምከው ቢጠፋም
ወዳጅ ፊቱን ቢያዞር፣ በውሎህ ባትረካ
አትዘን እንግዲህ፣ ከቶ አትቁረጥ ተስፋ…
አርቲስት ቴዎድሮስ ታደሰ “ዝምታ” በተሰኘ ሙዚቃው በህይወት አጋጣሚ መውደቅ እንዳለ፣ ተስፋ አስቆራጭ ነገር ሊያጋጥመን እንደሚችልና ወዳጆቻችን ጭምር ሊርቁን እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን በፍጹም እጅ መስጠትና ተስፋ መቁረጥ እንደማያስፈልግ መነሳሳትን ይፈጥራል፡፡ ልባቸው ለተሰበረ ሰዎች አይዞን በማለት አብሮነትን እና ወንድማማችነትን ያሳያል፡፡
እዚህ ጋር የአንጋፋውን ሙዚቀኛ ነዋይ ደበበን “አይዞሽ እህቴ” የተሰኘውን ሙዚቃም መጥቀስ ያሻል፡፡ የነዋይ ሙዚቃ ለእህቶች እና እናቶች ብርታት እና ውዳሴ የሚሰጥ እንዲሁም ሰዋዊ አብሮነትን የሚያጎላ ስራ ነው፡፡
አይዞሽ እህቴ
በርቺ እህቴ
ሀዘን መከራሽን ችግርሽን አልወድም
በሥራ ባህልሽ ድህነትሽ ያክትም ።
እንይሽ በደስታ በድል ውበት ደምቀሽ
ከችግር ድህንት በጥረት ተላቀሽ ።
እርቀሽ ብትሔጂ ሠው ሀገር ብትኖሪ
በሀገር በወገንሽ በባንዲራሽ ኩሪ
ችግር ያልፋልና መከራን ድፈሪ…ይላል ድምጻዊው፡፡
በሌላኛ የጥበብ ሥራ ገጣሚ ሰሎሞን ሞገስ “ከጸሃይ በታች” በተሰኘው የግጥም መድብሉ ውስጥ “የማነው እርቃኑ?” የሚል አንድ ግጥም አለው፡፡ ይሄ ግጥም ወንድማማችነትን አጉልቶ የሚያሳይ ግጥም ነው፡፡
እብድ ብጤ ነበር እዚያ ጎዳናው ላይ
ብጭቅጫቂ ለብሶ እርቃኑ የሚታይ
የሰውነት ፀጋው ሀፍረቱ ተጋልጦ
ይታይ ነበረ አጽም-አጥንቱ ገጥጦ
ወዲህ ይስቃሉ የሚያዩት ወንዶቹ
ሸሽተው ይሮጣሉ ቆነጃጅቶቹ
ይስቁ ነበረ-ይሳቁ ሁላቸው
የራሳቸው እርቃን መሆኑ አልገባቸው…
ከላይ በሰፈሩት ስንኞች ውስጥ ገጣሚው የአዕምሮ ታማሚው ግለሰብ ገላ ሰው በመሆኑ የራሳችን ገላ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ዘወትር በአደባባይ አይተነው እንደ ዘበት የምናልፈው ጉዳይ፣ ገጣሚው ግን ከዚህ ልማዳችን ባሻገር ስላለው ጉድፋችን ገልጦ ያስነብበናል፡፡ የምንስቀው በራሳችን ገላ እንጂ በሌላ እንዳልሆነ በመግለጽ አብሮነትና ወንድማማችነትን አጉልቶ ያሳያል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ረጅም የኪነ ጥበብ ታሪክ አላት፡፡ በዚህ ሁሉ ዘመን ኪነ ጥበብን በመጠቀም ስለ ህዝቦች አብሮነት ተሰርቷል፡፡ ስለ ፍቅር ተዘምሯል፡፡ ስለ ሀገር ፍቅርና መተሳሰብ ተገጥሟል፤ ፊልሞች ለእይታ በቅተዋል፡፡ ከእነዚህ የፊልም ስራዎች ውስጥ “ላቦረና” የተሰኘው የአማርኛ ፊልም ጎልቶ ይጠቀሳል፡፡
ይህ ፊልም ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት የመጣች አንዲት ነጭ ሴት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ጎብኝዋም ወደ ቦረና ታቀናለች፡፡ በዚያም ከአስጎብኝዋ ጋር ተላምዳ፣ ከሀገሬው ህዝብ ጋር ተወድዳ በአብሮነት ስትኖር ያሳያል፡፡
የጉብኝት ጊዜዋ አብቅቶ ወደ ሀገሯ የምትመለስበት ወቅት ይደርሳል፡፡ ወደ ሀገሯ ለመመለስ ሻንጣዋን ሸክፋ ተነሳች፡፡ ግን አብሮነቱ እንዳትለያይ አድርጎ በፍቅር አስሯት ነበር፡፡ መሄድ አልቻለችም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ወሰነች፤ በመጨረሻም እንዲህ ስትል ትሰማለች፡፡ “ሀገሩ የፍቅር ነው፤ በመተሳሰብና በፍቅር ልቤ ተሞልቷል፤ ይዤው የመጣሁትን ጥሩ ያልሆነ ሃሳብ በሰዎች ፍቅር እቀይረዋለሁ፤ ኢትዮጵያ በፍቅር የቆመች ሀገር ነች፤ የምኖረው በዚህች ሀገር ነው፡፡”
ጥበብ የህብረተሰብ እና የባህል ነጸብራቅ ነው። ጥበብ የውስጣዊ አስተሳሰብ፣ ስሜት እና ልምድ መግለጫ ነው። ራስን ለማንፀባረቅ ከመጠቀም ባሻገር ማህበራዊ ትስስርና ብሄራዊ ኩራት የሚሰማው፣ የሚተጋገዝ፣ የሚረዳዳና የሚተሳሰብ ትውልድን ለመፍጠር ሚናው አይተኬ ነው፡፡
በአጠቃላይ ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ስራዎች በባህሪያቸው ሰዋዊ ናቸው፡፡ ወንድማማችነትንና አብሮነትን አጉልተው ያሳያሉ፡፡ ሰውን ዋነኛ ነገረ-ጉዳይ አድርገው ስለሚነሱ ተጽዕኗቸው የቋንቋን ድንበር አሳብረው ይሻገራሉ፡፡ ምክንያቱም የጥበብ ስራዎች ለሰው ልብ እጅግ የቀረቡ በመሆናቸው ተጽዕኗቸው አንድ ማህበረሰብ ወይም አካባቢ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ የተከየነበትን ባህል፣ ቋንቋና አውድ ሳይገባን ዕሴትን እንድንጋራ፣ የወል ማንነታችን እንዲጎለብት፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲደረጅ ስለሚያደርጉ ትልቅ ትኩረት ይሻሉ።
በአብርሃም ገብሬ