አብሮነት በጥበብ መነጽር

ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች  ረቂቅ ተፈጥሮ አላቸው፡፡ የሰዎችን ስሜት ቆንጥጦ በመያዝና ወደ ራሳችን እንድንመለከት ማድረግ ይችላሉ። ወዳጅነትና ፍቅርን በዓለም ላይ እንዲደረጅ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ለሰዎች መተሳሰብንና መረዳዳትን በማጉላት፤ አብሮነትን አተልቆ በማሳየት እሴቱ እንዲዳብር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በማጉላት ረገድም አበርክቷቸው ወደር የለውም። እንዲሁም ብዝሃነት የአብሮነት ጌጥ መሆኑን በጥበብ ሥራዎች  በስፋት በማንፀባረቅ ይታወቃሉ፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍም በየዓመቱ በፈረንጆች ህዳር 16 ቀን የሚከበረው “ዓለም አቀፍ የአብሮነት ቀን”ን መነሻ በማድረግ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች በማህበረሰቦች መካከል አብሮነትን አጉልቶ በማሳየት ረገድ ሚናቸው እስከምን ድረስ እንደሆነ ልናስቃኛችሁ ወድደናል፡፡

ስለአብሮነት ቀን በጨረፍታ

ሙዚቃን ጨምሮ የጥበብ ሥራዎች ለአብሮነት ያላቸው አበርክቶ የጎላ ነው

አብሮነት ውበት ነው፡፡ አብሮነት መተጋገዝ ነው፡፡ አብሮነት ጥንካሬ ነው፡፡ ዓለም በመተጋገዝ፣ በመተሳሰብና በመረዳዳት የተሞላች ነች፡፡ አንዱ ሰው ያለ ሌላው ሊኖር አይችልም። የሰው ልጆች በጋራ ሲተጋገዙ ምድር ለኑሮ እየተመቸች፣ ለቀጣዩ ትውልድ በርካታ ገጸ በረከቶችን  የምታስተላለፍ፣ በፍቅር የተሞላች ትሆናለች፡፡

እ.ኤ.አ. በ1996 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ህዳር 16 ቀን ዓለም አቀፍ የአብሮነት ቀን እንዲሆን የወሰነውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ይህን ተከትሎ “አብሮነት ማለት የዓለማችን ባህሎች፣ ማንነቶች እና ሰው የመሆን መንገዶችን ማክበር፣ መቀበል እና ማድነቅ ነው” ይላል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ዕለቱን አስመልከቶ በይፋዊ ገጸ- ድሩ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ፡፡

አብሮነት የሌሎችን ሁለንተናዊ ሰብአዊ መብቶች እና መሠረታዊ ነጻነቶች እውቅና ይሰጣል። ሰዎች በተፈጥሮ የተለያዩ ናቸው፤ አብሮነት ግን በሁሉም የዓለም ክፍሎች ውስጥ ያሉ፣ በጋራ የሚኖሩ ማህበረሰቦችን በአንድነት አስተሳስሮ የሚያኖር ነው፡፡ ይህ አብሮነት ደግሞ በተለያዩ የጥበብ ስራዎች ተንጸባርቋል፡፡

ጥበብና አብሮነት

ጥበብ ማህበረሰብንና ሀገርን ያስተሳሰራል። ማህበራዊ መስተጋብርን ከፍ ያደርጋል፡፡  በአካል የማይገናኙ ሰዎችን ያቀራርባል፡፡ በጋራ የሚኖሩ ሰዎችን ቀናነትና መተሳሰብ ያጎላል፡፡ ግንኙነቶችንና ወዳጅነቶችን  ይፈጥራል።

የጥበብ ሰዎች ከራሳቸው ባህልና ቋንቋ ውጪ ያለውን ማንነትና አመለካከት እንዲረዱ ያደርጋል፡፡ ከሌሎች ሰዎች፣ ቦታዎች እና ሃሳቦች ጋር ፊት ለፊት ያገናኛል፡፡ ይህ ደግሞ ዓለምን ከራሳቸው ውጪ ማየት እንዲማሩ እና አብሮነትን እንዲያጠናክሩ ያደርጋል፡፡

ጥበብ ከተለያዩ ባህሎች የመጡ ሰዎች በሙዚቃዎች፣ በፊልሞች፣ ምስሎች፣ ስዕሎች እና ታሪኮች እርስ በርስ እንዲግባቡ እና እንዲረዳዱ ያግዛል። ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች እና ባህሎች ጋር የሚዛመዱት እና የሚተዋወቁት በጥበብ ስራዎች ነው።

ሳንጃይ ጃንጊድ የተባሉ  ምሁር እ.ኤ.አ. በ2022 “ጥበብ ማህበረሰብን በመቅረጽ ሂደት ውስጥ ያለው ሚና” በሚለው ጥናታቸው እንደገለጹት ጥበብ ብዙውን ጊዜ ለማህበራዊ ለውጥ ተመራጭ መሳሪያ ነው። ምክንያቱም አብሮነትን ያጎላል፤ መንግስታት የህዝቡን ግንዛቤ ለማሳደግ፣ አብሮነትን ለማጠናከር ስዕሎችን፣ ቅርጻ ቅርጾችን፣ ድራማዎችን፣ ፊልሞችን፣ ሙዚቃዎችን እና ግጥሞችን የሚጠቀሙትም ለዚሁ ነው፡፡

አብሮነትን የሚያጎሉ የጥበብ ሥራዎች በጨረፍታ

ሀገራችን ኢትዮጵያ ረጅም የጥበብ ስራዎች ታሪክ ያላት ሀገር ነች፡፡ በዚህ ሁሉ ዘመን ይህን በመጠቀም ስለ ህዝቦች አብሮነት ተሰርቷል፡፡ ስለ ፍቅር ተዘምሯል፡፡ ስለ መተሳሰብ ተገጥሟል፤ ፊልሞችም ለእይታ በቅተዋል፡፡ ባለቅኔዎች ስለ አብሮነት ተቀኝተዋል፤ ሙዚቀኞችም አዚመዋል። ለአብነትም ከሃገራችን እውቅ ሙዚቀኞች መካከል አንዱ የሆነው አርቲስት ብርሃኑ ተዘራ “ሰላም ያገር ሰው” ሲል ያቀነቀነው ሙዚቃው የጋራ እሴቶችን አጉልቶ በማሳየት፤ ለአብሮነትና ለመተሳሰብ አጽንኦት በመስጠት በቀዳሚነት የሚጠቀስ የጥበብ ስራ ነው፡፡ 

ሰላም ያገር ሰው ያገር ሰው

እንደው ያገር ሰው…

አንድ ማዕድ ገበታ ያገር ሰው

አብሮ የሚቆርሰው፡፡

እንደው ከምር ከምር ፣

እንደው ከምር…

እንዴት ያምርብናል ከምር

ተዋድደን ስንኖር…

አርቲስት ብርሃኑ በዚህ ተወዳጅ ሙዚቃው አብሮነትን አጉልቶ አንጸባርቋል፡፡ የእርስ በእርስ መከባበር፣ መዋደድና ብዝሃነት ውበት ነው ሲል ጥበባዊ በሆነ መንገድ አሳይቷል። የኢትዮጵያውያን ብዝሃ ባህልና ቋንቋ እንዳለ ሆኖ የወል እሴት እንዳላቸው “ቢለያይም ቋንቋው ደማችን አንድ ነው” ሲል አብሮነትን አጉልቶ አንጸባርቋል፡፡

አብሮነትን አጉልቶ በማሳየት የሚታወቀው ሌላኛው ሙዚቀኛ ተወዳጁ አርቲስት ንዋይ ደበበ ነው፡፡ ንዋይ “ሀገሬን አልረሳም” ሲል ያቀነቀነው ሙዚቃው በብዙ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የነገሰ ነው፡፡ በዚህ ሙዚቃው አብሮነትን አጉልቶ ለማሳየት የተጠቀመው የማህበረሰቡን የወል እሴቶችን ነው፡፡ የሃገር ፍቅር፣ የወል ታሪክና እሴት፣ የህዝብ ጀግንነትና ሃገር ወዳድነት የኢትዮጵያውያን የአብሮነት መሠረት ናቸው ሲል በሙዚቃው ይነግረናል፡፡

የዜማ የቅኔ የቀሳውስት ሀገር

የቅዱስ ገዳማት የታቦታት ደብር

ፋሲለደስ አክሱም የታሪክ ምስክር

መስቀል ጽላታችን የእምነታችን ምስጢር

ገዳማት መስጊዱ ሃውልታችን ሳይቀር

ሀገሬ ሰው ኧረ እንዴት ነው

ወፍ አራዊቱ ኧረ እንዴት ነው…

አብሮነትን አጉልቶ በማሳየት ረገድ ብዙ የሃገራችን ገጣሚያን ጥሩ ተምሳሌት ናቸው። ለአብነትም ገጣሚ እና ፀሐፈ-ተውኔት ደበበ ሠይፉን “የብርሃን ፍቅር (ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ)” በተሰኘው የግጥም መድብሉ “ከአክሱም ጫፍ አቁማዳ” እና “በትን ያሻራህን ዘር” የተሰኙ ግጥሞቹ አብሮነትን ከሌላ ማዕዘን የሚያሳዩ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው፡፡ “በትን ያሻራህን ዘር” የተሰኘው የገጣሚው ስራ በዚህ ምድር ስንኖር ለማህበረሰቡ አንዳች ነገር ማበርከት እንዳለብን ጥበባዊ በሆነ መንገድ ይነግረናል፡፡ አብሮነትን ከሚያጠናክሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ማህበራዊ ሃላፊነት መወጣትና ለምንኖርበት ማህበረሰብ አንዳች በጎ ነገር መስጠት ነው፡፡ ለዚህ ይመስላል ገጣሚው “በትን ያሻራህን ዘር” ያለው፡፡

…ወርውር

የእጅህን ዘገር

በትን!

ያሻራህን ዘር

ይዘኸው እንዳትቀበር።

በአጠቃላይ ጥበብ ሰዎች ሀሳባቸውን የሚገልጹበት እና ስሜታቸውን ለዓለም የሚያካፍሉበት ሁለንተናዊ መንገድ ነው። ከዚህ አንጻር ጥበብ ከትውልዶችና ከሌላው ማህበረሰብ መገናኘት የሚቻልበት፣ አብሮነትን ለማጠናከር የሚጠቅም ወሳኝ አማራጭ ነው።

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review