አትሌቲክሱን ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ከቀጣዩ አመራር ምን ይጠበቃል?

You are currently viewing አትሌቲክሱን ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ከቀጣዩ አመራር ምን ይጠበቃል?

አገራት በአህጉራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍታቸውን ከሚገልጡባቸው ማህበራዊ ጉዳዮች መካከል ስፖርት አንዱ ነው። ኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍታዋን ስታሳይ የቆየችው ስም እና ዝና ባተረፈችበት የአትሌቲክስ ስፖርት ስለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በውጤት ማጣት ሳቢያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ያለው ውጤታማነት እየቀነሰና ኢትዮጵያውያን በውድድሩ አሉበት ሲባል የሚኖረው ሞገስ የቀረው በጭላንጭል ነው፡፡

በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት ከ125 ዓመታት በፊት በትምህርት ቤቶችና በወታደራዊ ካምፖች በመዘውተር እንደተጀመረ ይነገራል። የአትሌቲክሱን ስፖርት በበላይነት የሚመራው ተቋም “የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን” በሚል መጠሪያ ከተመሠረተም ከ70 ዓመታት በላይ ሆኖታል። ፌዴሬሽኑ የሚመራው በየአራት ዓመቱ የሚመረጡ ፕሬዝዳንትና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ሲሆን በቀጣይ አራት ዓመታት የፌዴሬሽኑ አመራሮች ደግሞ ዛሬ ታህሳስ 12 እና በነገው ዕለት በሚከናወን የ28ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ምርጫ ይካሄዳል፡፡

እንደነ አትሌት አበበ ቢቂላ፣ ምሩጽ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረ ስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና ሌሎችን ጨምሮ ስማቸውን በደማቁ ያስጻፉ አንጋፋ አትሌቶችን ያፈራች አገር ነች ኢትዮጵያ፡፡ አትሌቲክስ የባህል ያህል የዳበረባት አገር ውድድሮች በሚካሄዱባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ከነበረችበት ስፍራዋ እየለቀቀች፣ ውጤት እየከዳት ቀጥላለች። በቀን ሁለቴ ልምምድ የሚሰሩና ለማራቶን በሳምንት 200 ኪሎ ሜትር እየሮጡ ለአገራቸው ድል የሚታገሉ አትሌቶቻችን ባሉበት አገር እንዴት ሲባል ከሚገባት ስፍራ ጠፋች? የሚለው ጥያቄ ደግሞ አፋጣኝ መልስ ያሻዋል። ለመሆኑ ከዚህ ችግር ለመውጣትና አትሌቲክሱን ወደ ውጤታማነቱ ለመመለስ ከቀጣዩ አመራር ምን ይጠበቃል? የሚለውን ጉዳይ መፈተሽ ደግሞ የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ ነው፡፡ 

በተለይም ከወራት በፊት በተከናወነው የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በምትጠበቅባቸው ርቀቶች ውጤት አለማምጣቷ፣  በውድድሩ ውስጥ ውዝግቦች መኖራቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወዴት እየሄደ ነው?  የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ችሏል። ይህም ብዙዎች ቀጣዩን ፕሬዝዳንትና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ በጉጉት እንዲጠብቁትና ከጉባኤውና ከአዲሱ አመራር መፍትሄ ይመጣል በሚል ወደዛ ማማተራቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ 

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድምጽ አሰጣጥ እንዴት ነው? የሚለውም ጉዳይ የብዙዎች ጥያቄ በመሆኑ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አሰራርና ደንብ መነሻ አድርገን ወደ ጉዳያችን እንንደርደር። የብሄራዊ ፌዴሬሽኑ አባል የሆኑት ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች፣ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር፣ የዳኞች፣ አሰልጣኞችና የአንጋፋ አትሌቶች ማህበር፣ የሙያ ማህበራት፣ እንደዚሁም ክለቦች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቀጣይ አራት ዓመታት አመራርን የሚወስኑ ይሆናል፡፡

በአገሪቱ ቀደምት ከሆኑት የስፖርት አደረጃጀቶች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተጠቃሽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ውድድሮች ያስመዘገበቻቸው አንፀባራቂ ውጤቶች ከአትሌቲክሱ ጋር የተያያዙ ለመሆናቸው አያከራክርም። አሁን ላይ ወሳኙ ጥያቄ ታዲያ አዲስ የሚመረጠው ፕሬዝዳንትና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያንን ውጤታማነት ከመመለስ አንጻር ያለበት የኃላፊነት ሸክም ምን ያህል ነው? ምንስ ላይ አተኩረው ቢሰሩ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ? የሚል ነው፡፡

የአትሌቲክስ ስፖርት ጋዜጠኛው ወርቅነህ ጋሻው ለዚህ ጥያቄ በሰጠው አስተያየት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምርጫ ለብዙ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ወሳኝ ቢሆንም ግን ሁሉም ጥያቄዎች በአመራር ምርጫ ብቻ የሚፈቱ አይደሉም ይላል። አትሌቲክሱ የገባበት ችግር ውስበስብ መሆኑንና ባለፉት ኦሎምፒኮች ተከታትለው የመጡ ችግሮች ተቀናጅቶ መስራት አለመቻል፣ የስልጠና እና የታክቲክ ችግር፣ ከድሮ አሰለጣጠን ጋር ተመሳሳይ መንገድ መሄድ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን ያነሳል፡፡

እንደዚሁም ተስማምቶና ተግባብቶ ያለመስራት፣ ለአትሌቶች ምቹ ሁኔታ አለመፍጠር፣ ለባለሞያዎች ነፃነት አለመስጠት ተጠቃሽ ችግሮች መሆናቸውንም ጠቁሟል። ቀጣዩ አመራር ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ለእነዚህ ችግሮች ቅድሚያ ሰጥቶ ከሰራ መፍትሄ ይኖራልም ሲል የአትሌቲክስ ስፖርት ጋዜጠኛ ወርቅነህ ያስረዳል፡፡

ግልጽ የሆነ ስትራቴጂ ማዘጋጀት፣ የስልጠና ማንዋል፣ የስልጠና ስታንዳርድ፣ ዘመኑን የሚመጥን ፍኖተ ካርታ፣ ከየት ተነስቶ ወዴት መሄድ እንደሚፈለግ ማዘጋጀት እንደሚገባ በጋዜጠኛው በቀረበው ሀሳብ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህሩ አሰግድ ከተማ ይስማማሉ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ እና አትሌቶች ለአገሪቷ ብራንድ ናቸው፡፡ ይህን አውቆ አትሌቱን እና ባለሙያዎችን አክብሮ አብሮ በመስራት አትሌቲክሱን በማዘመን ለአዳጊዎች እና ሌሎችም የተስተካከለ የአሰራር መንገድ በመፍጠር ያለንን መልካም ገፅታ ማስቀጠል ይገባናል፡፡ የአዲሱ አመራር የቅድሚያ ስራም ይህ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የአትሌቲክሱ አመራር ከቢሮክራሲ ስራ ተላቅቆ ከታች ጀምሮ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት ላይ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል በሚለው ሀሳብ ላይ ሁለቱም አስተያየት ሰጪዎች ይስማማሉ፡፡ “ጥሩ አሰልጣኝ ካለ ጥሩ አትሌት እንደሚኖር አምናለሁ” የሚለው ጋዜጠኛ ወርቅነህ ደግሞ የስፖርት ልማት ስራ ላይ ማተኮርና የአትሌት አሰልጣኞች ላይ መስራትም ለችግሩ ሁነኛ መፍትሄ ስለመሆኑ ያብራራል፡፡ በዚህ አስተያየት የሚስማሙት መምህር አሰግድም በተለይ የህፃናት ውድድሮችን በየትምህርት ቤቶች መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ አትሌቲክሱ የአሸናፊነት ስነ ልቦና እና የአንድነት ስሜት እያጣ ስለመምጣቱ የሚያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ ኢትዮጵያውያን በውድድሩ አሉበት ሲባል የነበረን ሞገስ ጠፍቷል፤ ይህ ትልቅ ውድቀትና ለአትሌቶችም የስነ ልቦና ፈተና እየሆነን መጥቷል ሲሉም ተናግረዋል። ስለሆነም ከዘልማድ አሰራር መውጣት ዘመናዊውን አሰራር መከተል ከአዲሱ የአትሌቲክሱ አመራር የሚጠበቅ ነው ብለዋል፡፡ በተለይም እንደ ጋዜጠኛ ወርቅነህ አስተያየት አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር የሚኖረው ግንኙነት ግልጽና ወቅቱን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል ይላል፡፡ 

ለአትሌቶች በቂ የመለማመጃ ቦታ አለመኖርና ሌሎችንም የተነሱ ችግሮች የቀጣዩ አመራር ሌላኛው የቤት ስራ ስለመሆኑ የሚያነሱት የስፖርት ሳይንስ መምህር አሰግድ በመላ አገሪቱ የአትሌቲክስ ስፖርትን በማስፋፋት ተተኪ አትሌቶችን በብዛትና በጥራት በማፍራት በአህጉርና በዓለም አቀፍ መድረኮች የአገርን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ መትጋት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመጥናትን ቦታ እንድትመለስ አትሌቲክስን እንደ እግር ኳሱ የህዝቡ የእለት ተእለት ጉዳይ እንዲሆን መስራት፣ የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች ወደ አትሌቲክስ እንዲመጡ፤ የአትሌቲክሱን ችግሮች እንዲያጠኑ እና መፍትሄ እንዲያመጡ ማመቻቸት ይገባል የሚለውም የባለሙያዎቹ የመፍትሄ ሀሳብ ነው፡፡

በቀጣይ የአትሌቲክሱን ዘርፍ ለማሻሻል መደማመጥ ያስፈልጋል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ “ብዙ ክብረ ወሰን የያዙ አትሌቶች አሉን፣ አስተዳደራዊ ችግሮች ከተፈቱ ውጤት የማናመጣበት ምንም ምክንያት የለም፤ ይህ የሚሆነው ግን አመራሮቹ ከእልኸኝነትና ከእርስ በእርስ ንትርክ ወጥተው መነጋገርና መስራት ሲችሉ ብቻ ነው” ብለዋል።

በእርግጥ ይህ ባለሙያዎች የሚያነሱት ጉዳይ የአገሪቱ አትሌቶችም በተለያየ ጊዜያት ሲናገሩት ተደምጧል፡፡ በ19ኛው የዓለም ሻምፒዮና በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች የተካፈለው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በተመለከተ አሉ ያላቸውን ችግሮችና መፍትሄ ነው ያለውን ጉዳይ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠበት ወቅት የተናገረው ለጠፋው ውጤት ፌዴሬሽኑ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ነው፡፡

የፓሪስ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤቱ አትሌት ታምራት ቶላ የቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአስረጅነት አንስቶ በሰጠው አስተያየት በወቅቱ ለተበላሸው ውጤት ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት አትሌቶች እንዳልሆኑ ገልጿል። “ለጠፋው ውጤት በዋናነት ኃላፊነት የሚወስደው እኛ ሳንሆን ፌዴሬሽኑ እና አሰልጣኞች ናቸው፣ ሁለቱ አካላት ተቀምጠው ካልተናጋገሩ ውጤቱ በዚሁ ይቀጥላል” ሲል ስጋቱን መናገሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጉባዔ በየዓመቱ ከሚያከውናቸው የስራ አፈጻጸምና እቅድ ሪፖርት ባሻገር በየአራት ዓመቱ የሚያካሂደው የፕሬዝዳንትና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ዛሬና ነገ ይካሄዳል፡፡ የብሄራዊ ፌዴሬሽኑ አባል የሆኑት ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እጩዎችን ልከዋል፡፡ አምስት ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለፕሬዝደንትነት ዕጩ ሲልኩ አትሌት ስለሺ ስህን እና ገብረእግዚያብሄር ገብረማሪያም እንዲሁም አቶ ዱቤ ጅሎን ጨምሮ በሌሎች እጩዎች መካከል የሚደረገው የፕሬዝደንት ቦታ ምርጫ ተጠባቂ ነው፡፡ አዲስ የሚመጡ አመራሮች ምን ያህል የአትሌቲክስን ችግር ይቀርፋሉ የሚለውን ደግሞ ብዙዎች በጉጉት የሚጠብቁት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን “አትሌቲክሱ በማን ይመራ” በሚል ርዕስ  ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩ እጩዎችን በቀጥታ ስርጭት እቅዳቸውን እንዲያቀርቡ ባደረገበት ወቅት እጩዎቹ ብንመረጥ እንሰራለን ያሏቸውን አንኳር ጉዳዮች አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደሚመጥናት ቦታ መመለስ፣ የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች ወደ አትሌቲክስ እንዲመጡ ስልጠና፣ ውድድር እና የማዘውተሪያ ስፍራ ማስፋፋት እንደዚሁም የስልጠና መንገዳችንን መከለስ። በተጨማሪም የአትሌቶችን የምርጫ መስፈርት ለስፖርቱ ግልፅ እና ፍትሐዊ ማድረግ፣ የፌዴሬሽኑን አደረጃጀት መከለስ አለበት፣ ከሩጫ በተጨማሪ የሜዳ ተግባራት ውርወራ እና ዝላይ ላይ በትኩረት መስራት፣ ከውድድር አስቀድሞ ግልፅ የሆነ የምርጫ መስፈርት ማውጣትና የአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን መመለስ እና አትሌቲክስ ላይ ያለውን የእድሜ ማጭበርበር ለመቅረፍ በዳታ የታገዘ ስራን እንሰራለን የሚሉት ጉዳዮች ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩ እጩዎች እንሰራቸዋለን ካሏቸው ዋና ዋና ስራዎች መካከል ይገኙበታል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review