AMN – ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ ጋይ ተወያዩ፡፡
በውይይታቸው በጋራ ተጠቃሚነት፣ በሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት መክረዋል።
አቶ አደም ፋራህ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮ-ቻይና ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የብልፅግና ፓርቲ አበክሮ እየሰራ ይገኛል።
ከቻይናው ኮሙኒስት ፓርቲ ጋር ያለው አጋርነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።
ሁለቱ ፓርቲዎች በስልጠና እና ልምድ ልውውጥ በጋራ ለመስራት ስምምነት መፈጸማቸውን አስታውሰው፤ በቅርቡ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችን ያካተተው ልዑክ በቻይና የነበረው ጉብኝትም የስምምነቱ ፍሬያማነት ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በቀጣይም የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቶች በስልጠና እና በልምድ ልውውጥ መርኃ ግብሮች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብልፅግና ፓርቲ ፍላጎቱ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቻይና ጠንካራ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ጠቅሰው፤ ይህ ግንኙነት በፓርቲ ለፓርቲም ሆነ በመንግስታዊ ወዳጅነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያድግ መንግስታቸው አበክሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ለዚህም የኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች እና ሠላምን ለማስፈን የተሰሩ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረው፤ ለአብነት ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር የተደረሰውን ስምምነት ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተደረሰው የአንካራ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንደሆነ መናገቸውን ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡