በ1915 ዓ.ም ነበር በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት አልጋ ወራሽ የነበሩት ልዑል ተፈሪ መኮንን (አፄ ኃይለስላሴ) የዘመናዊ ትምህርት ቤት ግንባታ እንዲካሄድ ትዕዛዝ የሰጡት፡፡ በቃላቸው መሰረትም የትምህርት ቤቱ ግንባታ ተጠናቅቆ ሚያዝያ 19 ቀን 1917 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሂደቱን ‘ሀ’ ብሎ ጀመረ፡፡ “ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት” በሚል ስያሜም ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ እንዲሁም አዳሪ ትምህርት ቤት በመሆን አገልግሏል፡፡
ትምህርት ቤቱ የማስተማር ስራውን ሲጀምር 30 አዳሪና 50 ተመላላሽ በድምሩ 80 ተማሪዎች ነበሩት፡፡ ይህ የትምህርት ተቋም በቅርቡ ስያሜውን ከእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ወደ “ተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ” መቀየሩን የኮሌጁ ዲን አቶ አብዱልበር መሃመድ ገልፀዋል፡፡
ዲኑ ታሪክን አጣቅሰው እንዳብራሩት፣ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከ1928 ዓ.ም እስከ 1933 ዓ.ም የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ለጣሊያኖች ብቻ መማሪያ በመሆን አገልግሏል፡፡ ከዚያ በኋላ የመማር ማስተማሩን የቀጠለ ሲሆን ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት ቤቱን በመሰረቱት በልዑል ተፈሪ መኮንን (አፄ ኃይለስላሴ) መጠራቱ ተቀይሮ፤ “እንጦጦ የቀለምና ቴክኒክ ትምህርት ቤት” በመባል ተሰየመ፡፡

በ1994 ዓ.ም ደግሞ የእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም በሚል ስያሜ ሲሰራ ቆይቶ በ1996 ዓ.ም ወደ ኮሌጅነት በማደግ ስያሜው እንጦጦ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ተባለ፡፡ በኋላም እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በመባል እስከ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በዚሁ ስም ሲጠራ ቆይቶ በአሁኑ ወቅት ኮሌጁ “ተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ” ለመባል በአዲስ አበባ ምክር ቤት ፀድቆ ስያሜውን ማግኘቱን ዲኑ ጠቁመዋል፡፡
አቶ አብዱልበር እንዳስረዱት፤ ስያሜውን መቀየር ያስፈለገበት ምክንያት ኮሌጁ የመቶ ዓመት ታሪክ ያለው እንዲሁም የተመሰረተው በተፈሪ መኮንን በመሆኑና ኮሌጁ ሲመሰረት በስማቸው በመሆኑ፣ የሰሩትን ስራ ለማስታወስ ነው፡፡ በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ እንዲሁም የቀድሞው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከኮሌጁ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ስያሜው እንዲቀየር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ ኮሌጁ በተለያዩ ጊዜያት ስያሜውን መቀየሩ ሲመሰረት የነበረውን ስም ከማጣቱ ጋር ተያይዞ የነበረውን ዝናና ታሪካዊነቱን በተገቢው መንገድ እንዳይገልፅ ሆኗል፡፡ የኮሌጁ አዲሱ ስያሜ ገፅታውን ከመገንባት አንፃር፣ የነበረውን ገናናነትና ታዋቂነት ለመመለስ ፋይዳ እንዳለውም ዲኑ አስረድተዋል፡፡
ዘመኑን የሚመጥን ቴክኖሎጂ በመጠቀምና ብቁ፣ ተወዳዳሪ፣ ችግር ፈቺ የሆነ የሰው ሀይል በማፍራት ለማህበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ ራስ ገዝ ኮሌጅ እንዲሆን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አብዱልበር ከወራት በኋላ የመቶኛ ዓመቱ የአልማዝ እዩቤልዩ ክብረ በዓሉን ለማክበር እና ተቋሙን ለማስተዋወቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ዘመን ተሻጋሪው የእውቀት ቤት በተለያዩ ሙያዎች ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን በማፍራት ሂደት ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ በሃገራችን አንቱታን ያተረፉ በርካታ ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎችንም አፍርቷል፡፡ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፉም ፍሬአማ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት በ11 የትምህርት ዘርፎች የተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን 3 ሺህ 668 ሰልጣኞችን በቀንና በማታ መርሀ ግብር እያሰለጠነ ይገኛል፡፡
በሰገነት አስማማው