AMN-ታህሣሥ 15/2017 ዓ.ም
“የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ሀሳብ የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
በአዲስ አበባ እየተከበረ በሚገኘው በዓል ላይ የተገኙት ‘ኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲሴብሊቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት’ (ECDD) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታሁን ስምኦን ፣ መንግስት እና ህብረተሰቡ አካል ጉዳተኞች የሚያጋጥማቸውን ችግር በመቅረፍ ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።
የአካል ጉዳተኞችን መብት የሚያስከብሩ አስቻይ ህጎች እና ፖሊሲዎች ሊቀረፁ እንደሚገባ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በተለይ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ህይወታቸውን መቀየር የሚያስችሉ ተግባራት ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል።
አስቻይ ህጎች እና ፖሊሲዎች መኖር አካል ጉዳተኞች አቅማቸውን እና ክህሎታቸውን በሚገባ እንዲጠቀሙ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም መንግስት ፣ አጋር አካላት፣ ባለድርሻዎች እና ህብረተሰቡ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የበዓሉ ዋና ዓላማ የግንዛቤ ችግሮችን መፍታት ነው ያሉት ደግሞ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ተወካይ አቶ ሲሳይ ጥላሁን ናቸው።
በትምህርት፣ በሥራ እድልና በመሳሰሉት መብቶች የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
እለቱ በሀገራችን ተግዳሮቶችን አልፈው ለስኬት ለበቁት እውቅና የምንቸርበት ነው ያሉት አቶ ሲሳይ የአካል ጉዳተኛ ማህበራትን ድምፅ መስማት፣ መደገፍ እና ለስኬት ማብቃት ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
በ‘ኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲሴብሊቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት’(ECDD) አስተባባሪነት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው”ምንጭ 6768″ የተሰኘ የአካል ጉዳተኞች ነፃ የድምፅና ፅሁፍ መረጃ መለዋወጫ የስልክ መረጃ ማዕከል ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አንፃር ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል።
መተግበሪያው ይፋ እንዲሆን ተቋሙ ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።
“ምንጭ 6768 ” የስልክ መረጃ ማዕከል አካል ጉዳተኞች ለአራት አመታት የድምፅ መልዕክት በነፃ እንዲለዋወጡ አስችሏል ነው የተባለው።
በዛሬው እለትም የፅሁፍ መልዕክት መላላክ የሚያስችል ሆኖ እንዲያገለግል ማድረግ ተችሏል።
“ምንጭ 6768 ” የስልክ መረጃ ማዕከልን ይፋ ለማድረግ ኢትዮ ቴሌኮም እና UNFPA ላበረከቱት የገንዘብ ድጋፍ በመድረኩ የእውቅና ሰርትፍኬት ተሰጥቷል።
በማሬ ቃጦ
All reactions:
1818