AMN – የካቲት 3/2017 ዓ.ም
አካታችነት በፅንሰ-ሀሳብ ደረጃ ሲታይ በብዙ ዓውድ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ ትንታኔዎችን ይይዛል፡፡ እንደ መነሻ ይሆነን ዘንድ ፅንሰ-ሀሳቡን ሊያብራሩልን የሚችሉ ትንታኔዎችን ስንመለከት አብዛኛዎቹ የሚጋሩት ሀሳብ አካታችነት በተለያዩ ደረጃዎች ሊገለጹ የሚችሉ ልዩነቶችን እና ብዘሀነትን እንደሚያስተናግድ የሚተነትኑ መሆናቸው ነው፡፡ ሆኖም ግን አካታችነት በዕድሜ፣ በጾታ፣ በዘር፣ በሀይማኖት፣ በኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ወዘተ የተለዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በአንድ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ ከማድረግም የዘለለ ፅንሰ-ሀሳብን ይይዛል፡፡
አካታችነት ልዩነቶች እና ብዘሀነት የሚስተናገዱበት ሂደት መሆኑን በመርህ ደረጃ ከተቀበልን እነዚህ ልዩነቶችና ብዘሀነት የሚገለጹበትን መንገዶች ማስተዋልና መፈተሽ ስለ ፅንሰ-ሀሳቡ ግንዛቤ እንዲኖረን ያግዘናል፡፡
በጥቅሉ መገንዘብ እንደሚቻለው ባህል የአንድ ማህበረሰብ የኑሮ ዘይቤ እና ፍልስፍናው የማህበረሰቡ መገለጫ ባህሪያት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ባህል የሰው ልጅ አስተሳሰብ ውጤት እንደመሆኑ መጠን ሀሳብና አስተሳሰብ የማህበረሰባችን አብሮ የመኖር ቁልፍ እሴቶች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም መሰረት ብዙዎቹ ሰው ሰራሽ ልዩነቶች የሚመነጩት ሀሳብና አስተሳሰብን መሰረት ባደረገ ልዩነት ነው ወደሚል አመክንዮ ለመሻገር ከላይ የተነሱት ሀሳቦች አመላካች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሚያ አዋጅ 1265/2014 አካታችነትን የሀገራዊ ምክክሩ የመጀመሪያ መርህ አድርጎ ደንግጓል፡፡ በመሆኑም ኮሚሽኑ ለዘለቄታው የሚበጁ ሀገራዊ የመፍትሄ ሀሳቦችን አካታች በሆነ መንገድ በምክክሮች ለማመንጨት ከተለያዩ የሀገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት እና ዲያስፓራው ጋር በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ኮሚሽኑ በሀገር ውስጥ ከመሰረታዊው የህዝብ መገኛ (ወረዳ) 10 የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የሕዝብ ሀሳቦች በአግባቡ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቶች እንዲወከሉ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡ ያንን ተከትሎም ልዩ ልዩ ተቋማትን እና ማህበራትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በማሳተፍ አጀንዳዎችን በ10 ክልሎች እና 2 የከተማ አስተዳደሮች ማሰባሰብ ችሏል፡፡ በቀጣይም ኮሚሽኑ በፌዴራል ደረጃ ከተለዩ ባለድርሻ አካላት እና ከዲያስፖራው ማህበረሰብ አጀንዳን እንደሚሰበስብ ይጠበቃል፡፡
ኮሚሽኑ በዚህ የአካታችነት አውድ ውስጥ ሲሰራ ነፍጥ አንግበው በጫካ የሚገኙትን ወገኖቻችንን ጨምሮ በሀገር ጉዳይ ላይ ይመለከተናል ለሚሉ አካላት በሙሉ የአብረን እንስራ ጥሪን ከማቅረቡም በላይ ያለምንም የደህንነት ስጋት ወደ ጠረጴዛ በመምጣት ስለሀገር የሚመክሩበትን ሂደትም ሲያመቻች ቆይቷል፤ እያመቻቸም ይገኛል፡፡
ኮሚሽኑ አካታችነትን የቁጥር ወይንም የኮታ ጉዳይ ብቻ አድርጎ ሳይመለከት የሀሳብ ብዘሀነት የሚስተዋልበትን ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ ኮሚሽኑ በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ የፖለቲካና የሀሳብ መሪዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች በምክክር ሂደቱ ተሳትፈው ሀሳባቸውን እንዲያሰሙ ጥሪውን አቅርቦ የብዙዎችን አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱ ነው፡፡ በተለይም ኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን ባከናወነባቸው የሀገራችን አካባቢዎች እጅግ አመርቂ የሆኑ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን ባለድርሻ አካላትም ንቁ ተሳትፎን በማድረግ የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን በነፃነት አሰናድተው ለኮሚሽኑ ማስረከባቸው ተጨባጭ ማሳያ ነው፡፡
ኮሚሽኑ ከዚህም በኋላ በሚያከናውናቸው የምክክር ሂደቶች ከማንኛውም የፖለቲካ እና የሀሳብ መሪዎች ጋር በጋራ ለመስራት አሁንም በሩ ክፍት መሆኑን እያስታወቀ በተለይም፦
በሀገራችን ሰላምን ለማስፈን እና አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት፣
የኢትዮጵያን ሀገረ-መንግስት በሀገር አንድነት ውስጥ ለመገንባት እና ለማስጠበቅ፣
ሀገር አቀፍ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በእጅጉ የሚያስፈልግ እና የሚበረታታ እንደሆነ ኮሚሽኑ በፅኑ ያምናል፡፡
በመሆኑም የሀገራችንን ሰው ሰራሽ ችግሮች በጋራ ለመፍታት መተማመንን መሰረት ባደረገ መልኩ እና በአካታችነት መርህ ተመካክረን ለሀገራዊ ችግሮቻችንን ሀገራዊ መፍትሔ ለማምጣት ጥረት ማድረጋችን ለነገ የሚተው የቤት ስራ አይደለም ሲል ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡