AMN – ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ አካታች የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተግባራዊ መደረጉ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት እያሳደገ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ ገለጹ፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገትና መዋቅራዊ ሽግግር መሳለጥ ሚናውን እንዲወጣ የሚያስችል አዲስ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ጸድቆ ሥራ ላይ ውሏል፡፡
ፖሊሲው የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እና ለዘላቂ የሥራ ዕድል ፈጠራ የጎላ አበርክቶ እንዳለው አመላክተዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲው ከ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ጋር የተጣጣመ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎች ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ ምርቶች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የሚያደርገውን ፖሊሲ አካታች እንዲሆን ተደርጎ እንደተሻሻለም ጠቁመዋል፡፡
የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ጨምሮ የዘርፉን ምርታማነት የሚያሳድጉ ስትራቴጂዎችና መመሪያዎች ጸድቀው ሥራ ላይ መዋላቸውንም ተናግረዋል፡፡
ዘርፉ የተቋማት ቅንጅትና ትብብርን የሚጠይቅ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣ ብሔራዊ የማኑፋክቸሪንግ አስተባባሪ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ተሳትፎ በማሳደግ ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት አድርጓል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡