“አየር ኃይል የታጠቃቸውን ትጥቆች በመጠገን፣ በማደስ እና በማሻሻል የግዳጅ ዝግጁነትን እያረጋገጠ ነው” – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

You are currently viewing “አየር ኃይል የታጠቃቸውን ትጥቆች በመጠገን፣ በማደስ እና በማሻሻል የግዳጅ ዝግጁነትን እያረጋገጠ ነው” – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

AMN – ኅዳር 20/2017 ዓ.ም

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ባስቀመጠው የሪፎርም አቅጣጫ መሠረት ከዘመኑ ጋር የሚዋጅ የተቋሙን የአሰራር ስርዓት በማሻሻል ሠራዊቱ የሚገነባበትን የግንባታ ስትራቴጂ ከማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ አደረጋጃጀቶችን በመፍጠር ተቋማችን ረጅም ርቀት መጓዙን በኢትዮጵያ አየር ኃይል 89ኛ የምሥረታ በዓል ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የጦር የኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይልም በተቋማዊ ግንባታ፣ በአደረጃጃት እና በአሰራር እራሱን እያሻሻለ የመጣ መሆኑን ጠቅሰው በሰው ኃይል ግንባታ ላይም ትኩረት በማድረግ የወቅቱን የቴክኖሎጂ ዕውቀት በመላበስ ፕሮፌሽናል ሠራዊት የመገንባት ሂደቱን እያቀላጠፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ማሳያው ከአስተሳሰብ አንፃር የተሰጠው ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮ ላይ እንዲያተኩርና ፕሮፌሽናል ሆኖ እንዲገነባ የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ የስራ ውጤቶች መመዝገባቸው የተናገሩት ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ የዛሬ ተመራቂ በራሪዎች፣ ተተኪ መኮንኖች፣ ቴክኒሺያኖች እና ምልምል የሠራዊት አባላትም የዚሁ ዓለማ አካል መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

አየር ኃይል ከሰው ኃይል ግንባታ ባሻገር የታጠቃቸውን ትጥቆች በመጠገን፣ በማደስ እና በማሻሻል የግዳጅ ዝግጁነትን የማሳደግ ስራ መስራቱን ገልጸዋል።

የሚሰጠውንም ግዳጅ በላቀ አፈፃፀም እያከናወነ የሚገኝ እና የሀገራችን የአየር ክልል የማይደፈርበትን የዝግጁነት ስራ በፅናት የተወጣ ስለመሆኑም አረጋግጠዋል።

አየር ኃይል የውጊያ መሠረተ ልማትን በማስፋፋትና በማዘመን እንዲሁም አዳዲስ ትጥቆችን በመታጠቅ የሚሰጠውን ግዳጅ ቀን ከሌሊት በአስተማማኝ ሁኔታ የመፈፀም ብቃቱን የማሳደግ ተግባራትን ማከናወኑንም ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል መከላከያ በምግብ ራስን ለመቻል ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ ስንዴ፣ ጤፍ፣ የጓሮ አትክልቶች፣ የወተት ላም፡ የስጋ እና የእንቁላል ዶሮ ምርት ውጤቶችን በማቅረብ ሠራዊቱ በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ችሏል ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዚህም የተቋሙን ዕቅድ በማሳካቱ የልማት ተምሳሌት ሆኖ በአገር መከላከያ ደረጃ ሽልማት ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

የዛሬ ተመራቂዎችም በብዙ ረገድ ውጤታማ እየሆነ በመሄድ ላይ ያለውን አየር ኃይል ለበለጠ የተልዕኮ አፈፃፀም ለማብቃት ትልቅ ኃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑን ተረድተው በፍፁም ኢትዮጵያዊ ስሜትና ቁርጠኝነት አገራቸውን ብሎም ተቋማቸውን እንዲያገለግሉ ማሳሰባቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review