AMN – ጳጉሜን 1/2016 ዓ.ም
አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ (ኤኤምኤን) በመረጃ የበለፀገ ማኅበረሰብን ከመፍጠር ባሻገር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሣሁን ጎንፋ ገለጹ።
ኤኤምኤን መጪውን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለሚያሳድጋቸው ሕፃናት እና ለአሳዳጊዎቻቸው የልብስ፣ የጫማ እና የገንዘብ ስጦታ አበርክቷል።
በተቋሙ ግቢ ውስጥ በተከናወነ መርሐ-ግብር ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት አቶ ካሣሁን፣ የአዲሱን ዓመት በዓል ዋዜማ ከምናሳድጋቸው ልጆቻችን ጋር ማክበራችን ትልቅ ደስታ ይሰጠናል ብለዋል።
ኤኤምኤን የመዲናዋ ሚዲያ እንደመሆኑ በበጎ ሥራዎች ለሌሎችም ምሳሌ መሆን እንደሚጠበቅበት ገልጸው፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን የማሳደጉ ሥራ ጅማሮ መሆኑን እንደሆነ ገና ብዙ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
ዛሬ ለሕፃናቱ እና ለአሳዳጊዎቻቸው የተደረገው የበዓል ስጦታም ከልብ የተደረገ እና ሕፃናቱ እንደሁላችንም በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ተሳቦ መሆኑን ነው የገለጹት።
በለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ሠልጥነው በጥቂት ወራት ውስጥ ራሳቸውን መለወጥ የቻሉ ወገኖችን እንደ ምሳሌ በማንሣት፣ “ሕይወትን መለወጥ ላይ መሥራት ብዙ እመርታዎችን የሚያስገኝ በመሆኑ ሁሉም ወገን በዚህ ረገድ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” ብለዋል።
አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በጎ ሥራዎችን እና ተደራሽነትን በማሳደግ ላይ በትኩረት እየሠራ ነው ያሉት አቶ ካሣሁን፣ የተቋሙ አመራሮች እና ሠራተኞች ይህን የተቀደሰ ሐሳብ የበለጠ እንዲያሳድጉ ጠይቀዋል።
አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ማሳደግ ከጀመረ 8 ዓመታት ያለፉት ሲሆን አሁን ላይ 12 ሕፃናትን ያሳድጋል።
ለሕፃናቱ እና አሳዳጊዎቻቸው ከተቋሙ ሠራተኞች በሚቆረጥ ገንዘብ በየወሩ ለእያንዳንዳቸው 1 ሺህ 400 ብር ድጋፍ ያደርጋል።
ሕፃናቱ 18 ዓመት እስኪሞላቸው እና ራሳቸው እስኪችሉ ድረስም በየወሩ የ200 ብር ተቀማጭ እንደሚቆረጥላቸው ኤኤምኤን የሚያሳድጋቸው ሕፃናት አምባሳደር ወ/ሮ ዝናሽ በቀለ ተናግረዋል።
ዛሬ የበዓል ስጦታ የተሰጣቸው ሕፃናት እና አሳዳጊዎቻቸው አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ እያደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በዮናስ በድሉ