የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ መረጃን በማድረስ ህብረተሰቡን ከማገልገል ባሻገር በተለያዩ መንገዶች ማህበራዊ ኃላፊነቶችንም እየተወጣ እንደሚገኝ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ተናግሩ፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ባሳለፍነው ሐሙስ በተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል የልደታ ቅርንጫፍ በመገኘት ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ማዕድ አጋርቷል። የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ተቋሙ በሚዲያ ስራዎቹ የትውልድ ድምፅ ሆኖ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ከመደበኛ ስራው ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱንም እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አመራሮቹንና ሰራተኞችን በማስተባበር ከ500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ማዕድ አጋርቷል፡፡
አቶ ካሳሁን በገለፃቸው፣ ተቋሙ ህዝባዊ ወይም ኃይማኖታዊ በዓላትን ብቻ ምክንያት በማድረግ ድጋፍ የሚደረገው በቂ አይደለም በሚል ተነሳሽነት አቅም በፈቀደ መጠን በየጊዜው የሌሎችን ድጋፍ የሚፈልጉ ወገኖችን ማገዝ አስፈላጊ በመሆኑ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ስንተባበር ትልቅ ስራ መስራት እንችላለን ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ለዚህ ደግሞ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሰራተኞችና አመራሮች ያደረጉት ማሳያ ነው፡፡ ትንሽ የሚመስሉ ነገር ግን ለተጠቃሚው ትልቅ ጥቅም የሚያስገኙ በጎ ስራዎችን ማድረግ ለህሊናም እረፍት ይሰጣል ሲሉ አክለዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የትውልድ ድምጽ ሆኖ ከማገልገል ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት ላይ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሽታዬ መሐመድ ተናግረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በራሱ ተነሳሽነት ወቅትን መሰረት ባላደረገ መልኩ በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መመገብ ለማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ ማጋራቱ ለሌሎችም አርዓያ የሚሆን ተግባር እንደሆነ አንስተዋል፡፡
በምገባው ተጠቃሚ ከሆኑት ወገኖች መካከል ወይዘሮ ብርሃን ወ/ሳሙኤል አንዷ ናቸው። ጉልበት በነበራቸው ጊዜ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ይተርፉ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን በእጅ ማጠር ምክንያት ሰርተው እራሳቸውን መመገብ ባለመቻላቸው የሰው እጅ ጠብቀው ለማደር መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ አቶ ጌቱ ሮባም በማዕከሉ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ እንደማንኛውም ሰው ሰርቶ መብላት ባለመቻላቸው ለችግር መዳረጋቸውን ጠቅሰው፣ ከማጣት የተነሳ ብዙ ጊዜ ሳይበሉ ያድሩ እንደነበረና የከተማ አስተዳደሩ እያከናወነው ያለው የምገባ መርሃ ግብር ከከፋ ችግር እንደታደጋቸው ገልፀዋል፡፡
አቶ ካሳሁን በበኩላቸው፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን እና ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ መረጃን በተገቢው መንገድ ለመዲናዋ ነዋሪዎች ከማድረስ ባሻገር የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን እየተወጣ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ የችግኝ ተከላ፣ የትምህርት ለትውልድ ድጋፍ፣ ህጻናትን መደገፍና ማሳደግ ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በማህበረሰብ ውስጥ እንደመኖሩ መጠን ድርብ ኃላፊነት እንዳለበት አውቆ በሚዲያ ረገድ የማስተማር፣ መረጃ የመስጠትና የማዝናናት ኃላፊነት እየተወጣ ሲሆን፣ በማህበራዊ ኃላፊነት ረገድም ሚናውን እየተወጣ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ተቋሙ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሲሳተፍ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ካሳሁን፣ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ፣ በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል እና ሌሎች ከተማዋ ክፍሎች ሰራተኞችን በማስተባበር የችግኝ ተከላ አድርጓል። የ2016 ዓ.ም አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርንም የተቀላቀለ ሲሆን፣ በመጭው ማክሰኞ ሐምሌ 23 ቀን 2016 ዓ.ም በእንጦጦ ፓርክ የችግኝ ተከላውን ያከናውናል ብለዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር ላይም ሲሳተፍ ቆይቷል፤ ለዓጼ ናዖድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የተለያየ መጽህፍት፣ 10 ኮምፒውተሮችን እና ለሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን በተለያዩ ጊዜያት አበርክቷል፡፡
የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሰራተኞች በየወሩ ከደመወዛቸው 1 በመቶ እንዲያዋጡ በማድረግ 12 የአቅመ ደካማ ቤተሰቦች ህጻናትን እያሳደገ እና 11 አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎችን እየደገፈ ይገኛል፡፡ ለእነዚህ ህፃናት የትምህርት ቁሳቁስ፣ በየበዓለት ጊዜ የአልባሳትና ጫማ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ይህ ድጋፍ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉና ወደ ፊት ራሳቸውንና ሀገራቸውን የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል፡፡
ተቋሙ ለእነዚህ ህጻናት 18 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ በዝግ አካውንት በየወሩ 200 ብር እያጠራቀመ ይገኛል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤት በማደስ ካሉበት አስቸጋሪ ሕይወት እንዲወጡ አድርጓል፡፡ በዚህ የክረምት ወቅትም ሰራተኞቹን በማስተባበር እስከ 10 የአቅመ ደካማ ቤቶችን ለማደስ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ ያለፈውን፣ የአሁኑንና የወደፊት ትውልድ የማስተሳሰር አቅም አለው የሚሉት አቶ ካሳሁን፣ “ለትውልድ ድምጽ” ለመሆን ከፍተኛ ሪፎርም እያደረገ ከሚገኝባቸው ስራዎች ውስጥ ከይዘት ስራዎች በተጨማሪ የማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣትም ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡
በቶለሳ መብራቴ