አዲስ አበባን ከወንጀል ድርጊት የፀዳች ለማድረግ የሰዎችን ሰላምና ደህንነት የሚያስከብር ዘመናዊ የፀጥታ ተቋም እየተገነባ ነው- ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ

You are currently viewing አዲስ አበባን ከወንጀል ድርጊት የፀዳች ለማድረግ የሰዎችን ሰላምና ደህንነት የሚያስከብር ዘመናዊ የፀጥታ ተቋም እየተገነባ ነው- ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ

AMN-ጥር 15/2017 ዓ.ም

አዲስ አበባን ከወንጀል ድርጊት የፀዳች ለማድረግ የሰዎችን ሰላምና ደህንነት የሚያስከብር ዘመናዊ የፀጥታ ተቋም እየተገነባ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ገለፁ።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እና የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከማዕከል እስከ ወረዳ ከሚገኙ አመራሮች ጋር የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሄደዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፣ አዲስ አበባን ከወንጀል ድርጊት የፀዳች ለማድረግ የሰዎችን ሰላምና ደህንነት የሚያስከብር ዘመናዊ የፀጥታ ተቋም እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ከተማዋ ከዚህ በላይ የህግ የበላይነት እና የዜጎች ሰላምና ደህንነት የሚከበርባት እንድትሆንና የተጀመሩ የልማት ስራዎችም ሳይስተጓጎሉ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከፌደራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እንዲሁም ሕብረተሰቡን በሰፊው በማሳተፍ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የአደባባይ በዓላት ሃይማኖታዊ ትውፊቶቻቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ማድረግ ተችሏል ያሉት ኃላፊዋ ለዚህም ከተለያዩ ተቋማት ጋር የቅንጅታዊ ስራው ሚና የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ባለፋት 6 ወራት በከተማዋ የወንጀል መጠን 48 በመቶ በላይ እንዲቀንስ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ከተማዋ የጀመረችው የኮሪደር እና ሌሎች የልማት ስራዎችን በመጠበቅና በማስጠበቅ የደንብ ማስከበር ባለስልጣን አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ፣ ህገ-ወጥ ግንባታ፣ በትምህርት ቤቶች አካባቢ አዋኪ ድርጊቶችን መቆጣጠርና ህግና ስርዓት በከተማዋ እንዲነግስ ለማስቻል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ውጤታማ ስራ ማከናወን መቻሉንም ገልጸዋል።

ይህንን ለማስቀጠልም ባለስልጣኑ ከተቋማት ጋር የጀመረውን ቅንጅታዊ ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በበኩላቸው፣ ተቋሙ ባለፉት ወራት በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል።

በዚህም ባለፋት 6 ወራት በከተማዋ የወንጀል መጠን ከ48 በመቶ በላይ እንዲቀንስ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በአፈፃፀሙ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እና ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከፍተኛ አመራሮች፣ የተቋሙ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከክፍለከተማ እስከ ወረዳ የሚገኙ አመራሮች ተገኝተዋል።

በመሀመድኑር አሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review