
AMN- ኅዳር 12/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባን ውብ ጽዱ እና ለኑሮ ምቹ የማድረግ ስራ የአንድ ወቅት ንቅናቄ ሳይሆን የዘውትር ተግባር መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
የብልጽግና ፓርቲን 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በማስመልከት “ህዳር ሲጸዳ” በሚል መሪ ቃል በመላው አዲስ አበባ የጽዳት መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመላው ከተማዋ 2.5 ሚሊየን ነዋሪ በድግግሞሽ በጽዳት ዘመቻ ላይ ሲሳተፍ መቆየቱን የተናገሩት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተካሄደ የጽዳት መርሃ ግብር ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን ውብ ጽዱ እና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን እና ውጤትም መምጣቱን ገልጸዋል።
ጽዳት የአንድ ወቅት ንቅናቄ ብቻ ሳይሆን የዘውትር ተግባር መሆን አለበት ያሉት ከንቲባ አዳነች በየቀኑ በቆሻሻ ላይ መዝመት አመቱን ሙሉም ከተማዋን ውብ እና ጽዱ ለማድረግ መስራት ይገባል ብለዋል።
በቀጣይ ከቆሻሻ ነጻ የሆነ ብሎክና ወረዳ እየተለየ እውቅና እንደሚሰጥም ከንቲባ አዳነች አስታውቀዋል።
በሰብስቤ ባዩ